በመጽሐፍ ቅዱሳችን አዲስ ኪዳን ተብሎ በሚታወቀው ክፍል ጅማሬ ላይ የምናገኛቸው አራቱ ወንጌላት (ማለትም የማቴዎስ ወንጌል፣ የማርቆስ ወንጌል፣ የሉቃስ ወንጌል እና የዮሐንስ ወንጌል) ስለ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ውልደት፣ ሕይወት፣ አገልግሎት፣ ሞት እንዲሁም ትንሣኤ ይተርኩልናል። የወንጌላቱ ፀሐፊዎች የክርስቶስን ሕይወት፣ ማንነቱንና አገልግሎቱን የገለፁበትን መንገድ ማወቅ፣ በጥበብ ሰጭው መንፈስ ቅዱስ እየተደነቅን የተፃፉትን መልዕክቶች የበለጠ ለመረዳት ያግዘናል። እስቲ ጥቂት ሃሳቦችን እንመልከት።
ማቴዎስ በወንጌሉ ኢየሱስን በዋናነት የሚስለው እንደ ንጉሥ ነው፤ ሲወለድ ንጉሥ፣ ሲሞትም ንጉሥ። ምዕራፍ አንድ ላይ ያለውን የትውልድ ቆጠራ እንኳን ካየን ያተኮረው ነገሥታቱ ላይ ነው። መጽሐፉ ሲጀምር ራሱ እንደዚህ ይላል፦ “የዳዊት ልጅ የአብርሃም ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ ትውልድ መጽሐፍ።” በማቴዎስ ወንጌል ስለ መንግስት ብዙ ተፅፎ እናገኛለን። ደግሞም መንግስት ካለ ህገ-መንግስት አለና ከምዕራፍ አምስት እስከ ሰባት የተራራው ስብከት ተበሎ የሚታወቀውን ክፍል ጨምሮ ሐዋርያው ስለመንግስቱ መመሪያዎች፣ ከመንግስቱ ዜጎች ስለሚጠበቀው አኗኗር በዝርዝር አስቀምጦልናል።
ወደማርቆስ ወንጌል ስንሻገር ኢየሱስ ክርስቶስን በዋናነት የሚስልልን እንደ አገልጋይ ነው። በወቅቱ ለነበሩ ዝቅ ያለ ስፍራ ለሚሰጣቸው ወይም ለአገልጋዮች ሲደረግ እንደነበረውም የኢየሱስ የትውልድ ሐረግ ራሱ መገለጽ አላስፈለገውም። ለተከታዮቹ የማገልገልን ታላቅ ፋይዳ ሲያስተምራቸውም እንዲህ አላቸው፦ “ማንም ከእናንተ ታላቅ ሊሆን የሚወድ የእናንተ አገልጋይ ይሁን “ (ማርቆስ 10፥43)።
ሉቃስ በወንጌሉ ያተኮረው ደግሞ ስለ ጌታችን የሰው ልጅነት ላይ ነበር። በሉቃስ ወንጌል የሚገኘውን የትውልድ ቆጠራ እንኳን ስንቃኝ ከማቴዎስ ለየት ባለ መንገድ መዘርዘሩ ብቻ ሳይሆን አዳምም መጠቀሱን እንመለከታለን (የሉቃስ ወንጌል 3)።
የሐዋርያው ዮሐንስ ወንጌል ዋና ትኩረት ደግሞ የኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅነት ላይ ነው። ትረካው ስለአምላክ ነውና የትውልድ ሀረግም አናገኝም። ገና ወንጌሉ ሲከፈት ጌታችን በመጀመሪያ እንደነበር፣ በእግዚአብሔር ዘንድ እንደነበር፣ ራሱም እግዚአብሔር እንደነበር፣ ደግሞም ሁሉ በእርሱ እንደሆነ፥ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ እንዳልሆነ በተዋቡ ቃላት ያበስረናል። በእርግጥም ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም፤ ስሙ የተባረከ ይሁን።
መልካም ንባብ!
Comentários