ጥቂት ስለ ሐዋርያው ሉቃስ፦ ስሙ ብርሃን ሰጭ ወይም የብርሐን ምንጭ ተብሎ ሊተረጎም ይችላል። በትውልድ ግሪካዊ በሙያው ደግሞ ሐኪም እንደነበር በቆላስይስ ምዕራፍ 4 ላይ ጳውሎስ "ባለ መድሀኒቱ ሉቃስ" ሰላምታ ያቀርብላችኋል በማለት ያስተዋውቀዋል።ከጳውሎስና ከዴማስ ጋር በሁለተኛው የሐዋሪያ ጉዞዉ አብሮት የአገለገለ ሲሆን የሐዋርያት ሥራ መልዕክትም ፀሐፊ ነው። ይሕ ወንጌል የተጻፈው ከ65-70 አ.ም. ነው ተብሎ ይታመናል። በ84 አመቱም ላመነበት ጌታና ለወንጌል ሕይወቱን ከፍሎ መስዋዕት እንደሆነ ይታመናል።
ምዕራፍ 1፥1-4፦ ይህ ወንጌል ቴዎፍሎስ ተብሎ ይጠራ ለነበረ ሰው የተጻፈ ሲሆን ስለዚህ ሰው ብዙ የሚታወቅ ነገር የለም። ምናልባትም ሉቃስ ክቡር ብሎ ስለሚፅፍ በሕብረተሰቡ ውስጥ የተከበረ ሰው እንደሆነ መገመት ይቻላል። ቴዎፍሎስ (የስሙ ትርጉም የእግዚአብሔር ወዳጅ ማለት ነው) ስለ ክርስቶስና ስለ ወንጌል የተወሰነ መረዳት የነበረው እንደሆነና ፀሀፊው ሉቃስ ስለ ጌታ የበለጠ እውቀት ይኖረው ዘንድ ሊፅፍለት እንደወደደ ከአፃፃፉ ስልቱ እንረዳለን። ከ5-25 መጥምቁ ዮሐንስ የካህኑ የዘካሪያስና የሚስቱ የኤልሳቤጥ የፀሎት መልስ ሆኖ እንዴት እንደተወለደ በጥልቀት ይተርካል። ዘካርያስና ኤልሳቤጥ ያለነቀፋ የነበሩ ልጅም ለማግኘት ብዙ የፀለዩ ቢሆንም በቀረው የአይሁድ ሕብረተሰብ ዘንድ በሀጢዐት ምክንያት መካን እንደሆኑ ተደርገው ይታዩ ነበር። ዘካርያስ በቤተ መቅደስ እያጠነ በነበረበት ቀን መልዐክ ተገልጦለት ‘ልጅ ትወልዳለህ፣ ስሙንም ዮሐንስ ትለዋለህ፣ በእግዚአብሔርም ፊት ታላቅ ይሆናል፣ በእናቱ ማሕፀን እያለም በመንፈስ ቅዱስ ይሞላበታል’ ብሎ እንደነገረው በኋላም ሚስቱ ኤልሳቤጥ እንደፀነሰች ያስነብበናል። ከ26-38 ሰዋዊ ነፍስ ስጋዊ ማንነትም ያልነበረው የአለማት ፈጣሪ ጌታ በእግዚአብሔር አብ ትዕዛዝ በኃጢአት ምክንያት የጠፋውን የሰውን ልጅ ሊታደግ ከድንግል ማርያም እንደሚወለድ ስሙም ኢየሱስ (አዳኝ)፣ የልዑል እግዚአብሔር ልጅ፣የአባቱን የዳዊትን ዙፋን የሚወርስ፣ በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘልዐለም የሚነግስ እንደሆነ፣ መልዐኩ ለድንግል ማርያም የምሥራች ቃል እንደነገራት ጌታም በመንፈስ ቅዱስ ሀይል እንደተፀነሰ እናነባለን። ከቁጥር 39-56 ባለው ክፍል የመጀመሪያው ታላቅ ክስተት ማርያምና ኤልሳቤጥ በተገናኙ ጊዜ ዮሐንስ በእናቱ ማህፀን ውስጥ መዝለሉና የእናቱ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልታ የጌታዬ እናት ብላ ስለ ማርያም መናገሯ ብቻ ሳይሆን መጥምቁ ዮሐንስ የጌታን ጌትነት ያወቀው ገና በማህፀን ሳለ መሆኑ ነው። ማርያምም "ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች እንደተናገረ ለአብርሐምና ለዘሩ ምሕረትን አድርጓል" በማለት መወደስ ታቀርባለች። መዝሙሩ ልክ ሐና ቀንዴም ከፍ ከፍ አለ ብላ እንዳለች ንጉሥ ዳዊትም በብዙዎች መዝሙሮቹ እግዚአብሔርን ከፍ እንዳደረገው ይሕም የማርያም ዝማሬ የአምላክን ትክክለኛ ፈራጅነትና ተራዳኢነቱን የሚያወድስ ውብ ዝማሬ ሆኖ ተገኝቷል። ከ57-79 ማርያም ወደ ቤቷ እንደተመለሰች መጥምቁ ዮሐንስ እንደተወለደ በግርዛቱ ቀንም ዘካርያስ እንደበቱ እንደተፈታና በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ትንቢታዊ የሆነ የቡራኬ ቃል እንደተናገረ ሉቃስ ይፅፋል። ስለክርስቶስ ትንቢታዊ ቅኔ ሲቀኝ "እግዚአብሔር ለአባቶቻችን እንደ ማለ ኪዳኑን አስቧል፣ መሲሑንና አዳኙን ለሕዝቡ ቤዛ አድርጎ ልኳል፣ እሱ የደሕንነት ቀንድ ከጠላቶቻችንም የሚያሳርፍ ነው። አንተ ደግሞ ይለዋል ልጁን ዮሐንስን የልዑል ነቢይ ትባላለህ መንገዱንም ትጠርጋለሕ የመዳንን እውቀትም ለሕዝብ ትሰጣለህ" ይለዋል። ዘካሪያስ የተናገራቸው ትንቢቶች በሙሉም ፍፃሜ እንዳገኙ ልብ እንላለን።
ምዕራፍ 2፥ከ1-24 ያለው ሃሳብ በማቴዎስ ወንጌል ማስታወሻ ስለተፃፈ ያንን ይመልከቱ። ከ24-36 ባለው ክፍል የእግዚአብሔርን ማጽናናት ሳያይ እንደማይሞት በመንፈስ ቅዱስ ተረድቶ በእምነት ይጠባበቅ የነበረው ስምዖን ክርስቶስን ተቀብሎ አቅፎት በታላቅ ሀሴትና ደስታ ውስጥ ሆኖ "ለእስራኤል ብቻ አይደለም ለሰዎች ልጆች ሁሉ ያዘጋጀኸውን ይህንን ማዳንሕን አይቻለሁና እንግዲህ ባርያህን በሰላም አሰናብተው ብሎ ካመሰገነ በኋላ ቁጥር 35 ላይ ደግሞ እናቱ ማርያም በልጇ ሞት ሊደርስባት ስላለው ስቃይ "በአንቺም ደግሞ በነፍስሽ ሰይፍ ያልፋል" ሲል ትንቢት ተናግሮ እንደነበር እናነባለን። ከቁጥር 36-52 የሐናን የትንቢት ቃል፣ የኢየሱስን የልጅነት አመታት በጥበብ በቁመት በሞገስ በእግዚአብሔርና በወላጆቹ ፊት ማደጉን ይነግረናል።
ምዕራፍ 3፥ከ1-20 በነቢዩ በኢሳይያስ ምዕራፍ 4፥ከ3-5 እንደተነገረውና በአባቱም በዘካርያስ እንደተተነበየው የእግዚአብሔር ቃል በምድረበዳ ወደ ዮሐንስ ከመጣ በኋላ "ልዑሉ ሊመጣ ነው፣ በእርሱና በእናንተ መካከል እንቅፋት የሆነ ነገር ሁሉ ይወገድ፤ ስለ ሐጢዐታችሁ ስርየት ንስሀ ግቡ፣ ተጠመቁም። በአንደበት የአብርሃም ልጆች ነን ማለታችሁ ረብ የለውም ይልቅ ለንሰሀ የሚገባ ፍሬ አድርጉ" እያለ በዮርዳኖስ ዙሪያ ሁሉ እንደመጣና ብዙዎች እንደተጠመቁ እናነባለን። ከቁጥር 21-38 የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ጥምቀትን፣በሰላሳ አመቱ አገልግሎት እንደጀመረ እንዲሁም የጌታን የትውልድ ሐረግ ያስነብበናል። በዚህ ስፍራ በሌሎች ወንጌላት ያልተጠቀሰውን በጥምቀቱ ጊዜ ጌታ ይፀልይ እንደነበር የሚነግረን ሉቃስ ብቻ ነው።
በምዕራፍ 4፥1-13 የጌታን በምድረ በዳ መፈተን ስናነብ የምንረዳው ከፍጥረት መጀመሪያ ጀምሮ በእግዚአብሔር ዙፋን ላይ የቀናው፣ አዳምን በሀጢዐት ምክንያት ከገነትና ይባረር ዘንድ ያደረገው ክፉ ዛሬም ከኃጢአት ስርየት ሊሆንልን የመጣውን ጌታ ሊፈትን ወደኋላ እንዳላለ ነው። ልክ አዳምን ባሳተበት የማስጎምዠት ፈተና ጌታን በብዙ ፈትኖታል። ቁጥር 13 ላይ እስከ ጊዜው ከእርሱ ተለየ የሚለው ቃል ገና ሊፈታተነው ደግሞ እንደሚመጣ የሚያመለክት እንደሆነ እንረዳለን። በቀጠሉት የጌታችን አገልግሎት አመታትም በጴጥሮስ ንግግር ውስጥ በመገኘት ሳይቀር ጌታ ወደ መስቀል እንዳይሄድ ያዘነ መስሎ ፈትኖታል። ሞትን ድል አድርጎ እስከተነሳበት ቅፅበት ድረስ ሠይጣን የሚቤዠንን ጌታችንን መፈተኑን እንደቀጠለ ታላቁ ፈተናውም ጌታ በመስቀል ላይ አባት ሆይ ብትወድስ ይህች ፅዋ ከእኔ ትለፍ እስኪል ድረስ ጣሩን ማብዛት እንደነበር እንረዳለን። ከ14-30 ኢየሱስ በናዝሬት ስለደረሰበት ተቃውሞ ነው። በአይሁድ ሐይማኖት ስርዓት እንግዶች በምኩራባቸው ሲመጡ እንደሚያደርጉት ጌታ የነብዩ ኢሳያስ ጥቅል መፅሐፍ ተሰጥቶት እንዲያነብ በተጠየቀ ጊዜ የቃሉ ባለቤት ራሱ የራሱን ቃል በገዛ አንደበቱ ከኢሳያስ 61 "የጌታ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ላይ ነው ለድሆች ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ቀብቶኛልና" በማለት ጀምሮ በመንፈስ ቅዱስ ሐይል እንደተሞላ፣በመንፈስ ድሆች ለሆኑና በሀጢአትም ለታሰሩ የደሕንነትን ምስራች እንዳመጣ፣ የተወደደችው የጌታ አመት የእስራኤል መፅናናት የሆነው የእርሱ መምጣት እንደሆነ የመፅሐፉ ቃልም ዛሬ እንደተፈፀመ የመሲሁ ቀንም እንደተገለጠ ከአንደበቱ በሚወጣው የፀጋ ቃል እስኪገረሙ ድረስ አነበበላቸው። ፀሐፊው ከቁጥር 31-49 የተለያዩ ፈውሶችን እንዳደረገ ነግሮን ይሕንን ምዕራፍ ይዘጋል።
ምዕራፍ 5፥1-11 ከጌታ ጋርና በጌታ መሆን በሰማያዊውም በምድራዊውም ማትረፊያ እንደሆነ የሚያስረግጥ ግሩም ክፍል ሆኖ ይገኛል። ጌታ ወደ ጌንሳሬጥ(የገሊላ) ባሕር በመጣ ግዜ ለሐዋርያነት የመረጣቸው እነ ጴጥሮስ ወደ ባሕር ተጥሎ አሳ ሳይሆን ጭቃና ሳር የሰበሰበ መረባቸውን ያጥቡ ነበር። ጌታም በታንኳይቱ ላይ ሆኖ ካስተማራቸው በኋላ ስምዖንን ወደ ጥልቁ ፈቀቅ በሉ ይሄ አሳ ለማጥመድ ቦታው አይደለም ብሏቸው እንዳዘዛቸው ባደረጉ ግዜ ብዙ አሶችን አጠመዱ። በአሳ ማጥመድ ሙያ እድሜውን ሙሉ የተካነው ጴጥሮስ ባየው ተዓምር ከመገረም ባለፈ የጌታን ስልጣን በፍጥረት ላይ ተመለከተ። በዚህ ስፍራ ከተአምሩ ባለፈ ጴጥሮስ የጌታ ንፅህናና ቅድስና የእርሱን ድካምና ሐጢዐተኝነት ጉልህ ስለአደረገውም ጭምር ነበር እባክህ ከእኔ ተለይ ያለው። ከንቱነቱና ሐጢያተኛነቱ የማይታወቀው ሰው ኢየሱስን የማያውቅ ሰው ነው። ጴጥሮስ ግን ድካሙን ማወቁ የጌታን ቅድስና ማወቅ አስቻለው ለዚሕም ነው ጌታን በፊትህ ልገኝ አይገባኝም ያለው። ከቁጥር 12 ጀምሮ የሚገኙት ተአምራት በቀደሙት የወንጌላት ምንባብ ማስታወሻዎች ተጠቅሰዋል።
ምዕራፍ 6 ከ1-19 ስላሉት ክፍሎች በማቴዎስ አስራ ሁለትና በማርቆስ ሁለት ማስታወሻዎች ላይ ማየት ይቻላል። ከቁጥር 20-49 ፀሐፊው ሉቃስ ጌታችን ለደቀመዛሙርቱ የሚሰጠውን ምክር ፅፎልናል። ከቁጥር 29-23 ባለው ክፍል አወዳዳሪ በሆነ የአፃፃፍ ስልትና ኢየሱስ ከተራራው ስብከት ጋር በሚመሳሰል መልኩ ከእርሱ ጋር ሕብረት ሊያደርጉ ለወደዱ ሁሉ ስለእኔ ስትሉ ብትደኸዪ ብፁዓን ናችሁ፤ በእኔ ዘንድ ሐብታሞች ናችሁና ሲል ጀምሮ በዚህ አለም መራባችሁ ብፅዕናችሁ ነው ከእኔ መንግስት ጥጋብን ታገኛላችሁና፤ ዛሬ የምታለቅሱ ብፁዓን ናችሁ በመንግስቴ የዘለዓለም ሳቅ ይጠብቃችኋልና፣ በዚህ ምድር ስለእኔ ብትጠሉና ብትናቁ ብፁዓን ናችሁ ዋጋችሁ በሰማይ ታላቅ ነውና ይላቸዋል። ከቁጥር 24-26 ባለው ክፍል ደግሞ እውነት ነው በዚህ አለም ሐብታም መሆን በራሱ ክፋት የለውም ነገር ግን ከመንግስቴና ከእኔ ከበለጠባችሁ ያኔ ለጥፋት ነው፣ በዚሕ ዓለም ሕይወት ከረካችሁ በወዲያኛው ዓለም ትራባላችሁ፣ ስለ መተላለፋችሁ የማትፀፀቱና የማታለቅሱ ከሆናችሁ ወየውላችሁ፤ ኋላ ታለቅሳላችሁና አለም ስለእናንተ በጎ በተናገረች ግዜ ስለምስጋናዋ እጅግ ተጠንቀቁ ምክንያቱም የአለም ሰዎች እንደ እነርሱ ያሉትን ያመሰግናሉ በኃጢአታቸውም አይወቅሷቸውምና ይለናል። ከቁጥር 27 እስከ 35 የማቴዎስ አምስትና ሰባትን ከቁጥር 36 እስከ 50 የማቴዎስ ሰባት አስርንና የማርቆስ ሰባትን ማስታወሻዎችን ማንበብ ያግዛል።
Comments