top of page
Search

የሉቃስ ወንጌል የምንባብ ማስታወሻ፦ ከምዕራፍ 7 እስከ 10

Updated: Jul 10, 2024

የሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 7፥1-10፦ ስለ መቶ አለቃው እምነት ከማቴዎስ ምዕራፍ ስምንት ማስታወሻ ማንበብ ይቻላል። ከቁጥር 7 እስከ 14 ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰዎችን ከሞት ካስነሳባቸው ተዐምራቶች የመጀመሪያው የሆነው ከሐዋርያት ጋር ናይን ወደምትባል ከተማ እየሄደ እያለ የመበለቲቱን ልጅ ከሞት ያስነሳበት ሲሆን የቀሩት ሁለቱ የኢያኢሮስ ሴት ልጅና አልዐዛር ናቸው። በዚህ ስፍራ ጌታ ባሏ የሞተባት፣ረዳቷ ልጇ ብቻ የነበረ፣ በሞቱ ተስፋዋ ተንጠፍጥፎ ያለቀባት፣ ፅልመት የጋረዳት፣ ምርጫዋ ከልጇ ቀድማ መሞት የነበረች እናት በሀዘን ተጎሳቁላ በማየቱ እንደራራላትና ልጇን ከሞት እንዳስነሳላት ሉቃስ ይነግረናል። ይህ ተዐምር ገደብ በተበጀለት በሰው እሳቤ፣ውሱን በሆነ የቋንቋ ክህሎት፣ተናግሮ በሚደክመው አንደበት እንዴት ሊገለጽ ይችላል? ከ15 እስከ 35 ባለው ክፍል የዮሐንስን ጥርጣሬ ለማስወገድ ጌታ በማንኛውም ድውይነትና በሞት ላይ በታላቅ መለኮታዊ ስልጣን እየሰራ እንዳለ ይነግሩት ዘንድ ሰዎችን ይልካል። ከቁጥር 28 እስከ 35 ባለው ክፍል ፈሪሳውያንና የብሉይ ኪዳን ሕግ አዋቂዎችነ አለማመንና አመፀኛነት ተመልክቶ በምሳሌ እንቢልታ ነፋን እንደ ሕፃናት ተደስታችሁ አልዘፈናችሁም፤ ታለቅሱ እነደሁ ብለን ሙሾ አወጣንላችሁ አላለቀሳችሁም፣ መጥምቁ ዮሐንስ (ሁለተኛው ኤልያስ) መጥቶ ነበር ጋኔን አለበት አላችሁት፤ በመጨረሻ የሰው ልጅ እየበላና እየጠጣ እናንተን መስሎ መጣ የቀራጮችና የሀጢዐተኞች ወዳጅ አላችሁት፤ ግራ እንደተጋቡ ሕፃናት የቱን ጨዋታ መጫወት እንደሚገባችሁ እንኳን አላወቃችሁም ይላቸዋል። ከቁጥር 36 እስከ 50 በማቴዎስ ምዕራፍ 14 ላይ የጌታን እግር በሽቶ የቀባችው ሴት ሐጢዐተኛ እንደነበረች ይገልፅልናል። በስምዖን ቤት መጥታ ለሐጢዐቷ ስርየትና ለበደሏ ይቅርታ በጌታ እግር ሥር በወደቀች ጊዜ ስምዖን ይሕ ሰው በእውነት ነቢይ ቢሆን ኖሮ መተላለፍዋን ባወቀ ነበር ብሎ ባሰበ ግዜ ስምዖንን በርሱ ዐይን ሐጢዐተኛ ተብላ ከተናቀችዋ ሴት ጋር እያወዳደረው ‘ይህች ሴት ያሳየችን ፍቅርና አክብሮት እንዴት ዝም ልል ይቻለኛል? ወደ ቤትህ ገባሁ እታጠብ ዘንድ ውሀ አላቀረብክልኝም፤ ራሴንም ዘይት አልቀባኸኝም እርሷ ግን ከገባሁ ጀምሮ ሽቶ ቀባችኝ። እግሬንም በፀጉሯ እያበሰች ሳመችኝ። ከአንተ የግብዝነት ጽድቅ ይልቅ የሷ የሐጢዐት ኑዛዜ በልጧል። ስለዚህ ብዙ ወዳለችና ብዙው ሐጢዐቷ ተሰርዮላታል’ ይለዋል።


ምዕራፍ 8፥1-3፦ ጌታ መሲሕና አዳኝ ብቻ አልነበረም የእግዚአብሔር መንግሥት የምስራች ሰባኪ፣ ወንጌላዊም ጭምር እንጂ።ተከታዮቹን እርሱ ወደ አባቱ በሚመለስ ጊዜ ወንጌልን እንዲሰብኩ እያሰለጠናቸው ነበር። ከደቀመዛሙርቱ ሌላ ብዙ ሰዎች ጌታን ተከትለውት ነበር። በተለይም ከተለያየ ደዌ እንዲሁም ከአጋንንት እስራት የተፈወሱት ሴቶች ያገለግሉት ነበር። ከነዚህም መካከል ጌታ ከሞት ሲነሳ የተገለጠላት ማርያም መግደላዊትና የጌታን ትንሣኤ ለደቀመዛሙርት የነገረችው ዮሐና ነበሩበት። ምዕራፍ 8፥5-15፦ ስለዘሪው ምሳሌ የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 13ን ማስታወሻ ያንብቡ። ቁጥር 10 ላይ "የእግዚአብሔርን መንግሥት ምስጢር ማወቅ ተሰጥቷአችኋል" የሚል ኃይለ ቃል አለ።የዚህን ቃል ጉልበት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ኤፌሶን ሰዎች በፃፈው መልእክቱ ምዕራፍ2፥11-22 እና ምዕራፍ 3፥1-6 እግዚአብሔር በልጁ በኩል በከፈለው ዋጋ አይሁዳውያንና አረማዊያንን እንዴት አንድ እንዳደረጋቸው ሲያስረዳ ይህንን እውቀት ከሰው አልተማርኩትም ይልቁንም እግዚአብሔር የዚሕን ታላቅ ምስጢር መገለጥ ሰጠኝ በማለት ፅፏል። ይሕ የእግዚአብሔር መንግ ሥት ምስጢር በመንፈስ ቅዱስ መገለጥ ሊታወቅ የሚችል እውነት ወይንም እውቀት ነው። የዚሕ ክቡር ምስጢር ተቀባይ ለመሆን በወንጌል ማመን ክርስቶስን መቀበል የግድ ነው ይሕ ካልሆነ ላላመኑ ሁሉ እውነቱን እያዪ ልብ የማይሉት እየሰሙትም የማያስተውሉት ይሆንባቸዋል። ከቁጥር 19 -21 እናቱና ወንድሞቹ ሊጎበኙት በመጡበት ጊዜ ጌታ ወንድሞቼ እነማን ናቸው ብሎ በማለቱ የተናገረበት መንገድ ያለአግባብ ሲተረጎም ኖሯል። ጌታ ይህንን ሲል በጭራሽ ቤተሰቦቹን በሚያቃልል መንገድ አልነበረም። ስጋዊ ቤተሰቦቻችን አስፈላጊ መሆናቸው እውነት ሆኖ ሳለ ከመንፈሳዊ ቤተሰቦቻችን ያስተሳሰረን የክርስቶስ ደም ህብረት ከሞት በኋላ የሚቀጥል ዘልዐለማዊ እንደሆነ ከማያምኑ ሥጋዊ ቤተሰቦችን ይልቅ ከሚያምኑ ወገኖቻችን ጋር የበለጠ ቀረቤታ ይኖረን ዘንድ የተገባ እንደሆነ ለማስረገጥ ስለፈለገ ብቻ ነው። ከቁጥር 21-56 ላሉት ክፍሎች የማቴዎስ 8 እና የማርቆስ 4 ማስታወሻዎችን ማየት ይረዳል።


ምዕራፍ 9፥1-6 የማቴዎስን ማስታወሻ ምዕራፍ 10፤ ምዕራፍ 9፥7-16 የማቴዎስን ማስታወሻ ምዕራፍ 14፤ ምዕራፍ 9፥17-22 የማቴዎስ ማስታወሻ ምዕራፍ 16፤ ምዕራፍ 9፥23-27 የማቴዎስ ማስታወሻ ምዕራፍ 17፤ ምዕራፍ 9፥28 -36 የማቴዎስ ማስታወሻ ምዕራፍ 17 ማንበብ ያግዛል። ከቁጥር 51-56 ሉቃስ ኢየሱስ ከሐዋርያት ጋር ወደ ሰማርያ ሲጓዙ ስለደረሰባቸው ተቃውሞ ይፅፍልናል። ሰማርያውያን በትውልድ አይሁዳውያን ቢሆኑም ከአረማውያን ጋር በመጋባታቸው አይሁድ ይንቋቸው ነበር። በዚህ ምክንያት ጌታንና ተከታዮቹን ተቀብለው ማስተናገድ አልፈለጉም ነበር። በዚህ የተከፉት ያዕቆብና ዮሐንስ በኤልያስ ዘመን እንደሆነው ጌታ ከሰማይ እሳት ወርዶ እንዲያጠፋቸው በጠየቁበት ወቅት "ለምን? እናንተ ሊኖራችሁ የሚገባው የእኔ መንፈስ ነው።እኔ ደግሞ ነፍስን ላድን እንጂ ላጠፋ አልመጣሁም በማለት ገስፆአቸዋል ምክንያቱም ሀሳባቸው የበቀልና የጥላቻ ሰለነበረ ነው። ከቁጥር 57-62 ኢየሱስን መከተል ዋጋ እንደሚያስከፍል የሚያስተምር ክፍል ነው። አንደኛው አባቴን አስቀድሜ ልቅበር ሌላኛው አስቀድሜ ቤተሰቤን ልሰናበት ብለው ምክንያት ይደረድራሉ።ጌታ ደግሞ ሙታኖችን ለሙታኖች ተውላቸው ገበሬ በሬዎቹን ጠምዶ ወደ ኋላ ካየ ትልሙን እንደሚስት ከወንጌልና ከእኔ የሚበልጥባችሁ ነገር ሁሉ ፍፃሜው ጥፋት ነው ይላቸዋል። ጌታን በፅናት ስለመከተል ሳስብ የቤተክርስቲያናችን መጋቢ ከአመታት በፊት በአንድ የእሁድ ስብከቱ ‘አንድ የአይሮፕላን አብራሪ ግማሽ ርቀቱን ካለፈ በኋላ ለመንገደኞቹ ከእንግዲህ ምንም እክል ቢገጥመን ወደ ፊት እንጂ ወደ ኋላ የማንመለስበት ርቀት (point of no return ) ላይ ደርሰናል እንደሚል ጌታን ይዘን ወደፊት መጓዝ አለብን፤ ክርስትና እንደ ገበጣ ጨዋታ ጠጠር አንስቶ ቢቀናኝ ገስጋሽ ቢከፋኝ ተመላሽ የምንለው አይደለም’ ሲል የተናገረውን አስታውሳለሁ።


ምዕራፍ 10 ከ1-24፦ በነዚህ ቁጥሮች ያለው ትምሕርት በማቴዎስ ማስታወሻ ምዕራፍ 10 ላይ ተዘርዝሯል። የተለየው ነገር ጌታ ከሐዋርያት በተጨማሪ ሌሎች ሰባ ሁለት ሰዎችን ጨምሮ ለአገልግሎት ማሰማራቱ ነው። እነዚህ ሰዎች ተመልሰው በመምጣት አጋንንት በስሙ እንደተገዙላቸው በነገሩት ግዜ "መናፍስት ስለተገዙላችሁ አትደሰቱ ይልቁንስ ደስታችሁ በእኔ በማመናችሁ፣በምትወርሱትም የአምላክ መንግስትና ሰማችሁ በሰማይ መዝገብ ስለተፃፈ ሊሆን ይገባል" አላቸው። ከቁጥር 25-37 የሙሴ ሕግ አዋቂና መምህር የነበረ አንድ ሳምራዊ ጌታን ለመፈተን የዘልዐለም ሕይወትን አገኝ ዘንድ ምን ላድርግ ብሎ በጠየቀው ግዜ ዘሌዋውያን 18፥5 ላይ "ስርዓቴን ጠብቁ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ የሚሰራ ቸው ሰው በእነርሱ በሕይወት ይኖራልና ስለሚል" ሕጉ በዚሕ ጉዳይ ላይ ምን ይላል" ብሎ ጌታ ይጠይቃል። ደጉ ሰው እንደሚገባ በመለሰ ግዜ ጌታ "በል ያንን አድርግ ይለዋል" ። ኢየሱስ እንዲህ ሲል የሰው ልጅ ሕግን በመጠበቅ ይድናል ማለቱ አይደለም፣ በእምነት እንጂ። ከሰው ልጆች መካከል አንድም እንኳን ሕግን ሙሉ በሙሉ መፈፀም ባለመቻሉ ነው ክርስቶስ የሕግ ፍፃሜ ሆኖ የመጣው።

13 views0 comments

Comments


bottom of page