በማርቆስ ወንጌል ምዕራፍ 12፥1-12 ባለው ክፍል የወይን ተክል ተክሎ ለገበሬዎች ስለአከራየው ሰው ምሳሌ ይናገራል። ተካዩ ሰው እግዚአብሔርን እርሻው ደግሞ የእስራኤል ወይም በወቅቱ የነበረው የእስራኤል ሕዝብ ምሳሌ እንደሆነ ይታመናል። ከብሉይ ዘመን ጀምሮ እስከ ጌታ መምጣት ድረስ እስራኤልና ሕዝቧ ፊታቸውን ወደ እግዚአብሔር እንዲመልሱና ያዘጋጀላቸውንም በረከት እንዲወርሱ እግዚአብሔር በተለያዩ ዘመናት የላካቸውን ነቢያቶቹን በድለዋል፣ አጎሳቁለዋል፣ ገድለዋል (2ኛ ዜና 24፥21)። ካሕኑ ዘካሪያስ “የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ ለምን ትተላለፋላችሁ? አይሳካላችሁም። እናንተ እግዚአብሔርን ስለተዋችሁት እርሱም ትቶአችኋል” ባላቸው ጊዜ በእግዚአብሔር ቤተመቅደስ አደባባይ ላይ በድንጋይ ወግረው ገድለውታል። በኢሳይያስ 5፥1-15 ላይ “ፍትሕን ፈለገ ደም ማፍሰስን አየ፣ ፅድቅንም ይተማመን ነበር፤ ግን የጭንቀት ጩኸትን ሰማ ስለዚህ እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ ለእጆቹ ስራ ክብር ስላላሳዩ ቁጣን አመጣ” እንደሚል ዛሬም ኢየሱስ ወደ አይሁድ በመጣበት ግዜ ንቀትን፣ሙግትን፣ክስንና ውንጀላን አበዙበት በዚህ ብቻም አላቆሙም ለገዳዮቹም አሳልፈው ሰጡት። እግዚአብሔርም ጌታን፣ ወንጌሉንና ሐዋርያቱን በመናቃቸው ማቴዎስ ምዕራፍ 21፥43 ላይ “የእግዚአብሔር መንግሥት ከእናንተ ተወሰዳ ፍሬዋን ለሚያደርግ ሕዝብ ትሰጣለች” ተብሎ እንደተጻፈው የእግዚአብሔር መንግሥት ከአይሁዳውን ተወስዳ በእምነት የአብርሃም ልጆች ለሆንነው ለእኛ ተሰጠች። ጌታችንም የተከበረ የአዲሲቷ ቤተመቅደስ የማዕዘን ድንጋይ ሆነ። እኛም አይሁድ የናቁትን ክርስቶስን በማመን የመዳንን በረከት መቀበል ብቻ ሳይሆን የአዲሱን ወይን እርሻ የምንከባከብ ፍሬያማ ገበሬዎች እንሆን ዘንድ ከኢየሱስ የወንጌል አደራ ተሰጠን። ከ13-17 ለቄሳር ስለሚሰጥ ግብር ከ18-27 በትንሳኤ ጊዜ ስለጋብቻ መኖር ወይም አለመኖር ለጌታ ከአይሁድ መሪዎች የቀረቡለትን አጥማጅ ጥያቄዎች እናነባለን። ጌታም ግብርን ለተገባው ለቄሳር እንዲሰጡ፣ የጋብቻም ዋነኛ አላማ እግዚአብሔር አምላክ ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሏት ብሎ በተናገረው ትዕዛዝ መሠረት ሞት በዚህ አለም እስካለ ድረስ የሰው ልጅ ዘር እንዳይጠፋ ትውልድ እንዲቀጥል እንደሆነ፣በትንሣኤ ግዜ ግን በራዕይ 21፥4 “እንባን ከአይናቸው ያብሳል ከእንግዲህ ሞትም፣ ሐዘንም ስቃይም አይኖርም” እንደሚል ጋብቻም ሞትም አይኖሩም። በጌታ የሆኑ ሁሉ በሰማይ እንዳሉ መላእክት ሆነው ለዘለዓለም ይኖራሉ ይላቸዋል።
ምዕራፍ 13፥1-23 ስለዘመኑ መጨረሻ ምልክቶች (የማቴዎስ ወንጌል ማስታወሻ ምዕራፍ 24 ይመለከቷል)፤ ከ24-27 ጌታ ስለዳግም ምጽአቱ ምልክቶች ይናገራል። ከ32-37 ስለ ጌታ ዳግመኛ መመለስ ከአብ በስተቀር የሚያውቅ ማንም እንደሌለ ከነገረን በኋላ ተጠንቀቁ ልክ እኔ ዳግመኛ ነገ እንደሚመጣ አይነት እያሰባችሁ እያንዳንዷን የሕይወት ቀናችሁን በጥንቃቄና በእግዚአብሔር ፈቃድ ውስጥ ኑሩት ይለናል። በዚሕ ስፍራ ሌላው በጥንቃቄ ልናየው የሚገባው ስለ ጌታ የምፅዐት ቀን ጉዳይ ነው። ጌታ ኢየሱስ በራሱ አንደበት ስለምፅአቱ ቀን ከአብ በቀር የሚያውቅ የለም ብሎ በመናገሩ በሌሎች ቤተ እምነቶች ዘንድ አምላክና ሁሉንም አዋቂ ሆኖ ሳለ አላውቅም ማለቱ ፈጣሪነቱን ጥያቄ ውስጥ ሲያስገባ ኖሮአል። ትልቁ እውነት ግን የእግዚአብሔር አብ አላማና እቅድ ከእግዚአብሔር ወልድ ወይንም ከእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ የተሰወረ አለመሆኑ ሊሰመርበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑ ነው። ጌታ በስጋ ሀጢዐት የሌለበት ከውድቀት በፊት የነበረው አዳም ምሳሌ ሆኖ በምድር ላይ ስለተገለጸና ለጊዜውም ቢሆን በፈቃዱ መተካከልንም ዕውቀቱንም ለእግዚአብሔር አባት ስለተወ እንጂ በሥላሴ ዘንድ የእውቀትንም የአምላክነትንም መበላለጥ ለማሳየት ፈልጎ አይደለም። ሌላው አሳሳቢ ነገር በምድራችን ላይ የጌታ ምጽአት መቃረቡን አመላካች የሆኑ ክስተቶች እውን እየሆኑ እንዳለ መነጋገሩ ተገቢ ሆኖ ሳለ ብዙ አማኞችና ሰባኪዎች ተገቢ ባልሆነ መልኩ ርቀው በመሔድ ክርስቶስ መቼ እንደሚመጣ ትንቢት ለመናገር ጥረት ሲያደርጉ ይደመጣል። ይሕ ፍፁም ስህተት ነው። ከላይ እንዳየነው የዚህን ዕውቀት ባለቤትነት ጌታችን ኢየሱስ ሳይቀር ለአብ ነው የተወለት። በጌታ የምፅአት ቀን ላይ ትንቢትና መገለጥ የሚመጣ ከሆነ የእምነት እንቅፋት ከመሆን ሌላ ረብነት የለውም። ይህ አይነቱ ትንቢትና መገለጥ ምናልባትም ወደ ድፍረት የቀረበ ይሆናልና መጠንቀቅ የግድ ነው።
ምዕራፍ 14፥1-11፦ የእስራኤልን ከግብፅ ባርነት ነፃ መውጣት ለማሰብ አይሁዳውያን በየአመቱ ፋሲካን ለማክበር ከሚዘጋጁበት ጥቂት ቀናት በፊት የካሕናት አለቆችና የሙሴ ሕግ (ብሉይ) መምህራን በቀያፋ ቤት ተሰብስበው በጌታ ላይ ቢያሴሩም በዚህ የበዓል ወቅት በትንሹ ከ50 ሺህ ሰው እስከ 200 ሺህ ሰው ለፋሲካ በኢየሩሳሌም ይሰበሰብ ስለነበር ጌታን ለመያዝ ቢሞክሩ ረብሻ ሊነሳ ይችላል ብለው ሰግተዋል። ጌታችን ደግሞ በለምጻሙ ስምኦን ቤት መዐድ ተቀምጦ ነበር። ማርታ የማርያምና የአልዐዛር እህት ውድ ሽቶ ይዛ መጥታ ብልቃጡን በመስበር የጌታን ራስና እግሩን ቀባችው። ይሕ የአልባስጥሮስ ሽቶ በዚያ ዘመን ዋጋው ሲሰላ ሶስት መቶ ዲናር ሲሆን ይሕም የአንድ ሰው የአመት ደመወዝን ያሕል መጠን ነበረው። ይሁዳና ሌሎች ስለ ሽቶው ውድነት ቢናገሩም ይህች ሴት ሽቶውን መስበር ብቻ አልበቃትም፤ አልፋ የሴት ልጅ ክብሯ በሆነው በፀጉሯ እግሮቹን አበሰችለት፤ የአምልኮዋ ጥግ ከንፈሮቿ የጌታን እግሮችና የመሬቱን አፈር እስከመንካት ድረስ ነበር። ከቁጥር 12-25 ማርቆስ የጌታ እራት ስርዓት ለመጀመሪያ ጊዜ በራሱ በኢየሱስ ትዕዛዝ እንደተፈጸመ ያስነብበናል። ለመሆኑ የጌታ እራት ምንድን ነው? ይህንን ሥርዓትስ ለምን እንፈፅማለን? የሚሉ ጥያቄዎች ሊነሱ ይችላሉ። የጌታ እራት ስርዓት ጀማሪው ራሱ ጌታችን ክርስቶስ ነው። የተከበረውም ከፋሲካ እራት ጋር ነበር። በአሮጌው ኪዳን በፋሲካ ወቅት በበጎችና በኮርማዎች ደምና ስጋ ለኃጢአት መስዋዕትና ለአይሁዳውያን ይቅርታና ስርየት የሚቀርብ ስርዐት የነበረ ሲሆን በአዲሱ ኪዳን የሚቀርበው የጌታ እራት (ስጋና ደም) ግን በጌታ ሞትና ትንሣኤ ላመኑ ሁሉ የሚደረግ ህያው የመታሰቢያ ስርዓት ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች በፃፈው አንደኛ መልዕክቱ ምዕራፍ 11፥23-34 በግልጽ እንደፃፈው የጌታ እራትን ስርዓት የምንፈፅምበት ምክንያት ከራሱ ከጌታ የተሰጠን ትዕዛዝ ብቻ ስለሆነ ሳይሆን ደሕንነትና የዘልዐለምን ሕይወት ያገኘነው በመስቀል በፈሰሰው የኢየሱስ ደምና ስጋ በመሆኑ የዚህ ኪዳን ተካፋዮች እንደሆንንና ጌታ ለእኛ ሲል እንደሞተ ከሙታንም እንደተነሳ ለመመስከር የሚያስቻለን፣ጌታ ዳግም እስኪመጣ ድረስ እንካፈለው ዘንድም የተሰጠን የመታሰቢያ ስርዐት ስለሆነም ጭምር ነው። ከ32-72 ድረስ ባለው ክፍል ማርቆስ ስለ ይሁዳና ጴጥሮስ ክህደት፣ በጌቴሴማኒ ስለነበረው የጌታችን የፀሎት ተጋድሎ፣ ለእኛ ለሐጢዐተኞች የተመደበውን ቅጣት ሊቀበል ነፍሱ ምንኛ ስቃይ ውስጥ እንዳለች፣ መፅናናትን በፈለገበት ግዜ ደቀመዛሙርቱ በእንቅልፍ እንደደከሙ፣ ኢየሱስ እንደተያዘ እንደተደበደበና ለክብሩ የማይገባ ብዙ ፀያፍ ነገር እንደተደረገበት ይነግረናል።
ምዕራፍ 15፥1-20 ጌታን በጲላጦስ ፊት ቀርቦ እንደተፈረደበት ያስነብበናል (የማቴዎስን ወንጌል ምዕራፍ 27 ማስታወሻን ይመልከቱ)። ከ21-32 ጌታ የራስ ቅል ወደተባለው ወደ ጎልጎታ ኮረብታ ተወስዶ ተሰቀለ። በሮማውያን ዘንድ ይህ ቅጣት በአመፀኛ ወንጀለኞች ላይ ይፈፀም የነበረ ሲሆን አላማውም የሚሰቀሉትን ሰዎች የስቃይ ጥግ ይሄ ነው ተብሎ ሊገለጽ የማይቻል እጅግ ዘግናኝ ወደሆነ ደረጃ ከፍ ለማድረግ ነው። በዚሕም ምክንያት የተሰቃዮቹን ስቃይ ለማስታገስና ሰውነታቸው እንዲደነዝዝ ከከርቤ ጋር የተቀላቀለ የወይን ጠጅ ይሰጧቸው ነበር። ጌታም ይሕንን በሰጡት ግዜ ለመጠጣት ፈቃደኛ አልነበረም። ተወዳጁ ለእኛ ሐጢዐት ለመሰዋት በፍፁም ከመፍቀዱ የተነሳ ያግዘው ዘንድ አንዳች ነገር አልፈለገም። ጌታ ከዚህ ሁሉ ስቃይ በኋላ ሕይወቱን ለእኛ ቤዛ አድርጎ ሰጠ። በጣም አሳዛኙና ልባችንን እየተጨመቀ እንዲደማ የሚያደርገው ነገር ጌታ በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 9፥58 ላይ ለቀበሮዎች ጉድጓድ ለሰማይ ወፎችም መሳፈሪያ አላቸው ለሰው ልጅ ግን ራሱን የሚያስጠጋበት የለውም እንዳለው በሕይወት በነበረበት ጊዜ ራሱን የሚያስጠጋበት እንዳልነበረው ሁሉ ከሞተም በኋላ የሰማይና የምድር ፈጣሪ መቀበሪያ አጥቶ የተቀበረው በሌላ ሰው መቃብር ውስጥ መሆኑ ነው።
ምዕራፍ 16፥1-8 ስለ ተወዳጁ ልዑል ትንሣኤ ይነግረናል። ስልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር የተሰጠው ጌታ አየሱስ ሕያውነትን ተላብሷል፤ አሁን ረቂቅ ሆኗል፣ ዳግም ለዘለዓለም አይሞትም። ሟች የነበርነውንም ሕያዋን አደርጎናል፣ ፍቅር ተስፋና የሕያውነት ምንጭ ሆኖልናል። መልዓኩ ሕያው ስለሆነ በሙታን መካከል ለምን ትፈልጉታላችሁ እንዳለ አስከሬኑ ተፈልጎ አልተገኘም። ከቁጥር 9 እስከ 20 ጌታ ለደቀመዛሙርቱ እንዲሁም ከአምስት መቶ በላይ ለሆኑ ሰዎች ታየ። ለተከታዮቹ ለዘለዓለም ድህነት የሆነውን የማይለወጠውን ቅዱስ ወንጌል ከፀሐይ መውጫ እስከ መጥለቂያው ድረስ በእጃቸው ላከው!
Comments