top of page
Search

የማርቆስ ወንጌል የምንባብ ማስታወሻ፦ ከምዕራፍ 6 እስከ 11

የማርቆስ ወንጌል ምዕራፍ 6፥1-6፦ በዚህ ምንባብ ውስጥ መፅሐፍ ነብይ በገዛ ሐገሩ አይከበረም እንዲል በገዛ ሐገሩ ብቻ ሳይሆን በገዛ ወገኖቹም ኢየሱስ ክብር የተነፈገው ሆኖ ይታያል። ዝቅ ለማድረግ በሚፈልግ መንፈስ ይሔ የዐናጢው የዮሴፍ ልጅ አይደለምን? እህቶቹስ ከእኛ ዘንድ አይደሉም እንዴ? ይሕን አይነት ተአምራት ሊያደርግ እንዴት ይችላል? እያሉ በመዘባበታቸው እንደተሰናከሉ እናያለን። ምቀኝነትና ቁጣ ስለበዛባቸው ጌታችንም በአለማመናቸው እየተደነቀና በክፋታቸውም እያዘነ ጥቂት ፈውሶችን ብቻ አድርጓል። ከቁጥር 7 እስከ 13 ባሉት ቁጥሮች ውስጥ እጅግ በጣም ጠቃሚ የሆኑ ክርስቲያናዊ ሀሳቦች ተከማችተዋል። የጌታ ሐዋርያት ከመምህራን ሁሉ በላቀው ጠቢብ መምህር ሰልጥነዋል፤ የተገባ የወንጌል ስንቅ ሰንቀዋል፤ ድውያንን የመፈወስና በክፉ መናፍስት ላይ ስልጣንን ተቀብለዋል፤ የቀረው ነገር ጥንድ እየሆኑ የጌታን ወንጌል ለመስበክ መውጣት ነው። ከመመርኮዣ በትር በቀር እንጀራም፣ ከረጢትም፣ ብርም፣ ትርፍ ልብስና ጫማ እንዳይዙ በአፅንኦት ተነግሯቸዋል። በቀረው ነገር ሁሉ በእግዚአብሔር መታመንና መደገፍ አለባቸው። መልዕክታቸውን ለመቀበልና እነሱን ለማስተናገድ ፈቃደኛ በሆኑ ሰዎች ቤቶች ብቻ እየገቡ እንዲስተናገዱና ተልዕኳቸው እስኪፈጸምም ድረስ በዚያ እንዲቆዩ፣ ወንጌሉን ካልተቀበሏቸው ሰዎች ቤት ሲወጡ የእግራቸውን ትቢያ አራግፈው ይወጡ ዘንድ ይሕም አብሯቸው የገባው የእግዚአብሔር በረከት እንዲወስድ ከማድረጉ ባለፈ የፍርድም ምልክት እንደሚሆን ተነግሯቸዋል (የሐዋ.ሥራ 13፥51)። ስለዚህ ነው በክርስቲያኖች አንደበት የሚነገረውን የክርስቶስን ወንጌል የናቁትን ቃሉ ራሱ ፍርድ ይሆንባቸዋል የመዳን ዕድል ፈንታቸውንም ያጣሉ።


ከቁጥር 14-29፦ የመጥምቁ ዮሐንስን አሟሟት ምክንያት፤ ከ30-44 ሴቶችና ሕፃናትን ሳይጨምር ጌታ አምስት ሺህ ሰዎችን እንደመገበ ይነግረናል። ከቁጥር 45-56 ባለው ክፍል ጌታችን ሁለት አስደናቂ ነገሮችን አድርጓል። በአራተኛው ክፍለ ሌሊት(ከሶስት ሰዓት እስከ ስድስት ሰዓት ከእኩለ ሌሊት በኋላ ነው) ሐዋርያት በማዕበል እየተገፉ በጭንቀት በነበሩት ወቅት የማዕበሉ ጌታ በውሀው ላይ እየተራመደ እንደመጣ እናያለን። ይህ የማይቻል ክስተት የልዑልን መለኮትነት፣ልዕለ ኃያልነቱን በፍጥረት ላይ ከፍተኛ ገዥነቱን ያመለከተ ብቻም ሆኖ አላለፈም፤ "እኔ ነኝ አትፍሩ" የሚለው የጌታ ሀይለ ቃል ወይንም አፅንኦት ያለው ድምጽ ተከትሎታል። በብሉይ ኪዳን እኔ ነኝ ከሚለው ከእግዚአብሔር መጠሪያ (ዘፀ.3፥13-15፤ ዘዳግ.32:39) ጋር ተመሳስሎነት ያለው ሆኖ እናገኘዋለን። ጌታ የምታዪኝ እኔ ክፉ መንፈስ አይደለሁም በማለት በስጋ የተገለጠ የእግዚአብሔር መለኮታዊ ማንነት ያለው አምላክ መሆኑን ለሐዋርያት እየተናገረ ነው። በዚህ ስፍራ ጌታ ሊረዳቸው ከመጣ በኋላ ሊያልፋቸው ለምን ወደደ? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ግድ ነው። አልፎ አልፎ እንደሚነገረው አለማመናቸውን አይቶ ነው ሊያልፋቸው የነበረው የሚለው ገለፃ መጨነቃቸውን አይቶ ሊረዳቸው መጣ በሚለው ቃል የሚፈርስ ከሆነ አሁንም ደጋፊ ሐሳብ በብሉይ ኪዳን ለመፈለግ እንገደዳለን። በዘፀአት 33፥19-22 ሙሴን መልካምነቴን በፊትህ አሳልፋለሁ፣ ክብሬ ባለፈ ግዜ፣ እስካልፍም ድረስ፣ ኢሳይያስን በተራራ ላይ ቁም አለው፤ 1ኛ ነገስት 19:11 እግዚአብሔርም አለፈ፣ የሚሉት ቁጥሮች ተጋግዘው በዚህ ስፍራ የጌታ ኢየሱስ የመለኮትነት ክብር እየተገለጠ እንዳለ ያስረግጡልናል።


ምዕራፍ 7፥1-23 የማቴዎስ ጥናት ማስታወሻ ምዕራፍ 15ን ወደኋላ ሄዶ ማየት ያግዛል። ጌታ በነዚህ ቁጥሮች ስር በጥቅሉ እየተናገረ ያለው አንዱን የእግዚአብሔርን ሕግ ለማፍረስ ድፍረት ይሆነን ዘንድ ሌላውን ሕግ መጠበቅን እንደመከላከያ ማቅረብ የለብንም። እግዚአብሔር ራሱን አይቃረንምና። አከበርን ካልን ሁሉን ሕግጋቶች በሙላት ልንጠብቅ ይገባል። ማንም አይሁዳዊ ውጫዊ ስርዓትን በመፈፀም ልቡን ንፁሕ ማድረግ አይችልም። ንፅህና ከውስጥ ወደ ውጭ ሊሆን ይገባዋል። የአባቶች ባሕል፣ ትውፊትና፣ ወግ በምንም ዓይነት የእግዚአብሔርን ሕጎች ሊሽር ወይንም ሊተካ አይችልም። ከቁጥር 24-37፦ በአገልግሎቱ ዘመን ጌታ እምነታቸውን ከመሰከረላቸው እንስቶች አንዷ ከሆነችው ከግሪካዊቷ ሴት ጋር ያደረገውን እጅግ አስደናቂ ምልልስ ያስነብበናል። ይሕቺ ሴት ከአይሁድ ያልሆነች ግሪካዊት ስትሆን ወደ ጌታ የመጣችው ለልጅዋ ፈውስን ፍለጋ ነበር። ጌታም እምነቷን ለመፈተን “ልጆቹ (አይሁዳውያን) በፊት ይበሉ ዘንድ ተይ የልጆችን እንጀራ ለቡችሎች (ለአረማውያን) መስጠት አይገባም” ባላት ጊዜ ጌታ ሆይ ውሾችኮ ከማዕድ ፍርፋሪ ይበላሉ አለችው። በኢየሱስ ዘንድ ትንሽ የሚባል ስጦታ የለምና ጌታም የእምነት ፅናቷን አይቶ ፈውስን ለቤቷ አደረገላት። የዕብራውያን ፀሐፊ 11፥6 ላይ "ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም" ዮሐንስ 1፥11-13 "ወደ ገዛ ወገኖቹ መጣ....ለተቀበሉት....ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ስልጣንን ሰጣቸው" እንዲል።


በምዕራፍ 8፥1-10 ጌታ ኢየሱስ ለሶስት ቀናት ከርሱ ጋር የቆዩ 4000 ያሕል ሰዎች መራብ ግድ ብሎት ምግብን ለሁለተኛ ጊዜ እንዳዘጋጀ እናነባለን። ርኅሩኅ የሆነው ጌታ ዳግም በሰባት እንጀራና በጥቂት አሳዎች አራት ሺህ ሰው ያህል መግቧል። ከቁጥር 11- 13 ፈሪሳውያን አሁንም ተጨማሪ ምልክቶችን ይጠይቃሉ። ጌታ ደግሞ ምልክት ቀድሞ ከመጣ እምነት ስፍራውን ያጣል ሰለዚህ ለዚህ ትውልድ ምልክት አይሰጠውም ምልክትን መጠየቅ ከአለማመን ጋር አንድ ነው ይላቸዋል። ከቁጥር 14-21 ደቀመዛሙርቱን ከርሱና በርሱ እስከሆኑ ድረስ ሊጎድልባቸው የሚችል ምንም ነገር እንደሌለ ያስተውሉ ዘንድ ይመክራቸዋል። ከ27-38 በብሉያት መፃህፍት እንደ ተጻፈው የዓለምን ሐጢዓት ሁሉ ለመሻር የበደል ዋጋ መስዋዕት ሆኖ ለመሞት የመጣ መለኮታዊ ፍቅር እንደሆነ ጌታ ይናገራቸዋል። በተለይም ከቁጥር 32 -38 ባለው ክፍል የክርስትና ትልቁ መርህ በግልጽ ተቀምጦ እናገኘዋለን። የስጋ ስራ የነፍስን ጬኸት ማፈን ነው። የነፍሳችን ከፍተኛ ጥሪ እግዚአብሔርን መፈለግና ማስደሰት መሆን አለበት። ለአለማዊ በረከቶች ቅድሚያ በሰጠን ቁጥር ክርስቶስ በሕይወታችን ይሰራ ዘንድ እንከለክለዋለን። ክርስቶስንና አለማዊ ስኬትን በተጓዳኝ ማስኬድ አይቻልም አንዱን መምረጥ የግድ ነው። ለዚህ አለም ግዚያዊ ደስታ ስንል ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ዘልዓለማዊ ሕይወትስ ለምን እናጣለን? በመሰረቱ ለአማኞች የአለም ኑሮአቸው ስኬት መለኪያ በጌታና ከጌታ ጋር የመሆናቸው ጉዳይ ነው። እግዚአብሔር ያለው ሰው ደግሞ ምንም አጣሁ ሊል አይችልምና። ዘማሪው ዳዊት ያለምክንያት አልነበረም በልዑል መጠጊያ የሚኖር ሁሉን በሚችል አምላክ ጥላ ውስጥ ያድራል ያለው።


ከዘጠኝ እስከ አስራ ስድስት ባሉት ምዕራፎች ውስጥ የተፃፉትን አብዛኞቹን የመልዕክቱን ክፍሎች በማቴዎስ ወንጌል ማስታወሻችን ላይ በዝርዝር አይተናቸው ነበር። በቀጣዩ ማስታወሻችን የተወሰኑትን አለፍ አለፍ እያልን እንመለከታለን።


ምዕራፍ 9:1-28 ማርቆስ የጌታን መልክ መለወጥ፣ የብላቴናውን ከዲዳነት መንፈስ መፈወስ ካስነበበን በኋላ በቁጥር 29 ላይ በመንፈሳዊ ሕይወት ውስጥ ስለጾምና ፀሎት ጠቃሚነት ይናገራል። ፀሎት በእግዚአብሔር ፊት የሚቀርብ የክርስቲያኖች መስዋዕት ነው።ለአምላካችን ክብር መንበርከክ ያለ ቋንቋና ንግግር አንተ ታላቅ ነህ ብሎ ማወጅ ነው። ለእግዚአብሔር የሚቀርብ እውነተኛ ፀሎት የስበት ሕግና የሕዋ ርቀት ሳይወስነው ወደ እግዚአብሔር ዙፋን ይደርሳል። ፀሎት የክርስቲያኖች የሀይል ምንጭ የሚሆነውም ከእምነት ጋር ጥምረት ሲኖረው ነው። ከፀሎት ጋር ያልተቀናጀ እምነት ውጤት አልባ ነው። እምነታችን ከፀሎት ጋር ከተጣመረ ግን የእግዚአብሔር ክንድ ይነሳ ዘንድ ምክንያት ይሆናል። የጌታን የጾምና ፀሎት ተጋድሎ ልብ ልንል ይገባል። ጾምም እንዲሁ በብዙዎቻችን ዘንድ ለተወሰነ ጊዜ ካለመብላት ጋር ተያይዞ ይነገራል። አለመመገብ የጾም አንዱ ክፍል ቢሆንም ካለመብላት ያለፈ ትርጉም አለው። የአምላካችን ፈቃድ በሕይወታችን እንዲፈፀም ሰውነታችንን ከምግብና ከመጠጥ ማቀብ እስከመቻል ድረስ ለጌታ ፈቃደኝነታችንን የምናሳይበት መንገድ ስለሆነ። ከቁጥር 42-50 ባሉት ቁጥሮች ጌታ ስዕላዊ በሆነ መንገድ ገሀነምን በቃላት ይስልልናል። ዳግም ደሕንነት ከቶ የማይገኝበት የስቃይ፣ የልቅሶ፣ የማይጠፋ እሳትና፣ የማያንቀላፋ ትል ያለበት ገዥው ርሕራሔ ቢስ የሆነበት ስፍራ ነው ። ስለዚህ አካል ተቆርጦ ከወደቀ ተመልሶ እንደማይቀጠል (እጅህን ቁረጣት የሚለው ቃል በግነት እየገለፀ ያለው በሀጢዐት ላይ ቁርጠኛ ውሳኔ ማድረግ እጅግ ጠቃሚ መሆኑን ነው) አማኞችም ሀጢዐትን ችላ ሳይሉ በንሰሀ፣ በይቅርታና በቁርጠኝነት ከሕይወታቸው ማስወገድ አለባቸው። ትንሽ ፍሳሽ ትልቅ መርከብ ታሰጥማለች እንደሚባለው ሐጢዐት ስር ሳይሰድ ካልተወገደ ለነፍስና ለሕይወት መጎሳቆል ምክንያት ሊሆን ይችላል።


ምዕራፍ 10 ከ1-12 ሰለ ፍቺ ፀያፍነት፣ ከ 13-16 ስለ ሕፃናት ተወዳጅነት፣ ከ17-31 ሕግን ሁሉ እንደሚገባ ጠብቆ በጌታ የመጨረሻ ጥያቄ ልቡ አዝኖ ስለሔደው ሐብታም ያስነብበናል። ጌታ በቁጥር 25 ላይ ለሀብታም የጌታ መንግሥት ምንኛ ሩቅ እንደሆነ የመርፌ ቀዳዳን ትንሽነት ከግመል ግዝፈት ጋር በማወዳደር ይናገራል። ሐዋርያው ጳውሎስ 2ኛ ቆሮ 8:9 ላይ ጌታችንን ሐብታም ሆኖ ሳለ በርሱ ድሕነት እኛን ባለፀጎች ሊያደርግ ስለእኛ ድሀ ሆነ እንዳለው የሁሉም ነገር ባለቤት የሆነው ጌታ መንግሥት ወራሾች ስለሆንን ከአለም ሀብትና ስኬት ይልቅ ጌታን ብለን ሁሉንም ከተውንና ሁለንተናችን ለርሱ ክብር ከተሰጠ እነደ እኛ ሀብታም አይኖርም ምክንያቱም ለእኛ ረብ የነበረውን ሁሉ ስለ ክርስቶስ ስንል እንደጉዳት እንቆጥረዋለንና ጌታም ይህንን መሰጠታችንን አይቶ ይረሳ ዘንድ ሰው አይደለም።


ምዕራፍ 11፥1-11 ትሁቱ ጌታ እንደ ምድራዊ ነገስታት በፈረስና በሰረገላ ሳይሆን በአሕያ ውርንጭላ ተቀምጦ ወደ እየሩሳሌም ገባ። የሚከተሉት ሕዝብም ሆሳዕና በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው እያሉ እየዘመሩ አጅቡት። ሆሳዕና የእብራይስጥ ቃል ሲሆን ትርጓሜውም መዳን ማለት ነው። ይሔ መዝሙር በአይሁድ ፋሲካ ወቅት የሚዘመር መሆኑም ጌታ ለኃጢአት መስዋዕት ቤዛ ሊሆን እየተዘጋጀ እንዳለ አመላካች ነው። ከ12-26 በቤተ መቅደስና ፍሬ አልባ በነበረችው የበለስ ዛፍ ላይ ስለተገለጸው የጌታ ቁጣ እናነባለን። ወቅቱ የበለስ ዛፍ ፍሬ የሚያፈራበት ግዜ አልነበረም፤ አንዳች ቢገኝባት ብሎ ጌታ መጣ በለሷ ግን ፍሬ አልባ ነበረች። ጌታም ከአሁን ጀምሮ ለዘላለም ማንም ከአንቺ ፍሬ አይብላ ይላታል። በመፅሐፍ ቅዱስ በለስ የእስራኤል ምሳሌ ሆና ትወሰዳለች(ኤርምያስ 8-13 /29-16፤ ሚክያስ 7-1)። ንጉሷ በመጣበት ወቅት እስራኤል እንደ በለሷ ቅጠል ውጭዋ ለምልሟል፤ በውስጧ ግን ፍሬ አልባ ነበረች። ከዚሕም ባለፈ እስራኤል የክብርን ንጉሥ እንደ መሲሕና አዳኝ አልተቀበለችውም። ለሞት አሳልፋ ልትሰጠው ተዘጋጀች እንጂ። ቤተመቅደሱም የታቦቱ ማደሪያ የህዝቦችም የፀሎት ቤት መሆን ሲገባው እንደ በለሷ ዛፍ ከውጭ ሲታይ ያማረ ውስጡ ግን በወንበዴዎችና በገንዘብ ለዋጮች የተሞላ ሆኖ ተገኘ። ለዚህም ይሆን በሰባ ዓ.ም ኢየሩሳሌም በሮማውያን ሠራዊት የፈራረሰችው?

14 views0 comments

Comments


bottom of page