top of page
Search

የማቴዎስ ወንጌል የምንባብ ማስታወሻ፦ ምዕራፍ 11-13

በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 11 ከጅማሬው እስከ ቁጥር 11 ጌታ ለመጥምቁ ዮሐንስ ጥያቄ የሰጠውን መልስ እናያለን። መነሻ ሀሳቡ ያለው ዮሐንስ በእስር ሆኖ ስለጌታ አገልግሎት ትክክለኛውን ዜና ስላልሰማ የጠበቀው መሲሕ አይሁዳውያንን ከሮማውያንና ከሄሮድስ እጅ ለምን ነፃ አላወጣም ብሎ በማሰቡና መጠራጠር በመጀመሩ መልዕክተኞች ወደ ጌታ እንደላከ ነው። ጌታም አደርጋለሁ ያለውን እያደረገ እንዳለ በኢሳይያስ 35፥5-6 የተነገረው የመሲሑ ትንቢት እየተፈፀመ እንደ ሆነ ብቻ ሳይሆን ዮሐንስ እውነተኛ ነቢይ እንዲያውም የበለጠ ነብይ እንደሆነ ይመሰክርለታል። በመጽሀፍ ቅዱስ ውስጥ ለመረዳት ከባድና ሞጋች የሆነው ጥቅስ ያለው ቁጥር 12 ላይ ነው። ይህም፦ "ከመጥምቁ ከዮሐንስ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ መንግስተ ሰማያት ትገፋለች ግፈኞችም ይናጠቋታል" የሚለው ነው። ይህ ጥቅስ ግፈኞች እንዴት ነው የሚናጠቋት? ለሚለው ጥያቄ በር ከፋች ሆኖ ተገኝቷል። ግፈኞች የሚለው ቃል ግፉአን፣ የተበደሉ፣ በብርቱ ፈተና ያሉ፣ በሚጋፋ አለም ፀንተው የሚቆሙ፣አምላካችንን ብለው ሙጥኝ ያሉ፣የእርሱን መንግስት በብርቱ ለማግኘት የሚዋጉ፣ የጠላትን ዕልህ የሚያስጨርስ እምነት ያላቸው፣ በእምነት ምክንያት ለሚመጣባቸው ነገር ሞት ቢሆን ሕይወት ወደኋላ የማይሉ፣ እነርሱ ሊወርሷት ይናጠቋታል ማለት ነው። በሉቃስ ወንጌል 16 Page 2 of 2 ቁጥር 16 ላይ ሁሉም ወደእርሷ በሀይል ይገቡባታል በማለት ለዚህ ጥቅስ አጋዥ መልስ ይሰጣል። ከቁጥር 26 እስከ 29 ጌታ እየተናገረ ያለው ንግግር ማንነቱን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው።እግዚአብሔርን ለማወቅ በእግዚአብሔርም መታወቅን ለማትረፍ የሰው ልጆች ሁሉ እኔን ማወቅ አለባቸው፤ በአባቴ እቅፍ የነበርኩ (ዮሐንስ 1:18)፣ አባቴ ማን እንደሆነ የማውቅ እውነተኛ ምስክር እኔ ብቻ ነኝ። ስለዚህ የደከማችሁ፣ ሸክማችሁ የከበደባችሁ ወደ እኔ ኑ ከእኔም የሕይወትን ቃል ተማሩ ነፍሳችሁ የዘለዓለምን ሕይወት፣ ስጋችሁም እረፍትን ታገኛለች እያለ ነው። ከራሱ ከእግዚአብሔር መጥቶ ስለ እግዚአብሔር እንድናውቅ ያደረገን ራሱ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን። አሜን!


ምዕራፍ 12 ከቁጥር 1 እስከ 14 ላይ ፈሪሳውያን የሕጉ ሰጪና ፈፃሚ የሆነውን ጌታ በሰንበት ቀን ደቀመዛሙርቱ እሸት ቀጥፈው ስለበሉ እርሱም የፈውስ ስራ ስለሰራ በመሞገት በቀን ሊወስኑት ሲሞክሩ እናነባለን።ጌታ እያለ ያለው ከስፍራና ከግዜ ቁጥጥር ውጭ የነበርኩት እኔ በገዛ ፈቃዴ ነው በግዜ የተወሰንኩት፤ ይሁንና በበዓልና በሰንበት ቀን መልካም ማድረግ ሀጥያት የለውም። የብሉይ ሕግ እውቀታችሁ የታለ? ዳዊት በሰንበት ያውም በቤተ መቅደስ የነበረውን ህብስት መብላቱንስ ምነው ረሳችሁ?

ብታውቁስ እኔ ከቤተመቅደስም እበልጣለሁ እንዳላቸው እንማራለን። በዚህ ምዕራፍ እንደሁልጊዜው ጌታ በምሳሌ መልኩ ስለ መልካምና ክፉ ዛፍ ፍሬ ይናገራል። በእምነት ሆነን ስንኖር ከሚጠበቁብን ማንነቶች አንዱ የመልካም ቃላት ባለቤቶች መሆናችን ነው። ቃላቶቻችን የሚያንፁ፣ ንፁህ፣ ውብና በጎ ሲሆኑ የልባችንንም ውበት ይናገራሉ። ከአንደበታችን የሚወጡ አፍራሽ ቃላቶቻችን ከወንድሞቻችን በፊት የሚያሳዝኑት እግዚአብሔርን ነወ። እሱ ብቻም አይደለም ከቃላችን የተነሳ ልንፀድቅ ወይንም ልንኮነን እንችላለንና። ከከንቱ ንግግሮቻችን የተነሳ ክፋትን፣ ፀብን፣ ጥላቻን እየዘራን የሚጎመዝዝ ሕይወት እንዳንኖር መጠንቀቅ ይኖርብናል።


በምዕራፍ 13 ከቁጥር 1 እስከ 58 ጠቢብ የሆነው ጌታ በምሳሌና በንፅፅሮሽ በማይረሳ መልኩ ልብ ብለው ለሚሰሙ ሁሉ ጥልቅ የሆነ መሰረታዊ የሆነ የእምነት አስተምህሮ ያስተምራል። የጀመረው ከ1-23 ስለዘርና ስለዘሪ፣ ከ24-43 ስለእንክርዳድና አረም፣ ከ44-52 ስለተደበቀ ሀብት ምሳሌ ነው። ዘሪው ጌታ፣ እርሻው የሰው ልጆች ሁሉ፣ ብዙ የሚያፈሩት የመንግስቱ ልጆች እንክርዳድ ዘሪው ዲያብሎስ ናቸው። መልካሙ ዘሪ ጌታችን ይበቅልለት ዘንድ አንድ ዐይነት የሆነ ዘር ዘርቷል። ፍሬያማ የሆነው በመልካምና ዘሩን ሊቀበል በተዘጋጀው መሬት ላይ የወደቀው ነው። የዘሩ እህል መልካም የነበር ቢሆንም ለቀሩት ዘሮች መምከን ትልቅ ምክንያት የሆነው ደግሞ የወደቁበት ስፍራ ምቹ አለመሆኑ ነበር። በጌታ ኢየሱስ የተዘራውየእግዚአብሔር ዘር (ቃል) የመንግስተ ሰማይ ዘር ነው። ይህ ዘር ይበቅል ዘንድ የዋህና እንደመልካም መሬት ሊያፈራ የተዘጋጀ ልብ ይፈልጋል። ምንም እንኳን ገበሬው ጠቢብ፣ ዘሩም የተመረጠ ቢሆንም የሚቀበለው ሠው ልብ አመፀኛ ከሆነ ፍሬያማውን የእግዚአብሔር ቃል ያመክናል።

24 views0 comments

Comments


Commenting has been turned off.
bottom of page