top of page
Search

የማቴዎስ ወንጌል የምንባብ ማስታወሻ፦ ምዕራፍ 17-20

በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 17 ከቁጥር 1 እስከ 13 ባሉት ክፍሎች ፀሀፊው ቀድመው ከታዩት ተዓምራዊ ክንውኖች የላቀውን የጌታን መልክ መለወጥ፣ ሙሴና ኤሊያስ ከጌታ ጋር ሲነጋገሩ፣ አብ አባት ስለተወዳጁ ዳግም በእርሱ ደስ የሚለው የሚወደው ልጁ እንደሆነ የመሰከረበትን ክስተት ያስነብበናል። በራዕይ 14:1 "በጉ በፅዮን ተራራ ቆሞ ነበር" እንዲል በዚህ ተራራ ላይ እጅግ የሚያስደንቅ ታላቅ ነገር ተከናውኗል። እግዚአብሔር፣ ጌታ ኢየሱስ፣ ሙሴና ኤሊያስ ተገኝተዋል።ደመናው የሕያው አምላክን ክብር፣ ኢየሱስ የእግዚአብሔር የማዳን ስራ ፈፃሚ፣ሙሴ የብሉይ ኪዳን ሕግ ተቀባይና የእስራኤል ነፃ አውጪ፣ ኤሊያስ ነቢያትንንና ትንቢቶቻቸውን ወክለው። ሙሴ በዘፀዓት 33፥18-23 ጀርባዬን ታያለህ ፊቴን ግን አታይም፣ ኤልያስ በ1ኛ ነገስት 19፥9 በእሳቱ፣ በምድር መናወጥና በብርቱ ነፋስ ውስጥ ሲያልፍ ያላዩትን ያልተሸፈነውን የእግዚአብሔርን ፊት በኢየሱስ ማየትና ከእርሱም ጋር በገሀድ መነጋገር ሆነላቸው። ይህ ብቻም አይደለም፤ ሉቃስ 9፥31 ላይ በግልጽ እንደተፃፈው "በኢየሩሳሌም ሊፈፀም ስላለው ስለ መውጣቱ ይናገሩ ነበር" እንደሚል የኢየሱስ የመስቀል ሞት እየቀረበ እንደሆነ መረዳት ይቻላል።


በምዕራፍ 18 ከቁጥር 1 እስከ 6፦ ሐዋርያት በመንግሥተ ሰማያት ስለሚገኝ ትልቅነት በጠየቁት ግዜ እንደሁልጊዜው ጌታ በእርሱ የሚያምኑ ሊኖራቸው ስለሚገባ ማንነት ሕፃናትን ምሳሌ አድርጎ ይናገራል (ጌታ በሚናገርበት የአረማይክ ቋንቋ ሕፃን የሚለው ቃል አገልጋይ ከሚለው ቃል ጋር ተመሳሳይ ፍቺ አለው)። ሕፃን፦ በጉልበቱ ትንሽ እንደሆነና አጋዥም እንደሚያስፈልገው የሚያውቅ፣ የማያስመስልና ራሱን የሆነ፣ የዋሕና ቅን ደግሞም የሚያምን ነው። ስለዚህ በአካል ብታድጉም በመንፈስ እንደዚህ ህፃን ከሆናችሁ እኔን ባለማመን ከሚመጣው ጥፋት ትድናላችሁ በመንግስቴ ከፍ ያለ ስፍራ አላችሁ ይላቸዋል። በቀጣዮቹ ክፍሎች መሰናክል ሆነው ከመንግስቱ ሊያጎሉን ከሚችሉ መተላለፎች ለመጠበቅ የምናደርገው ጥንቃቄ የአካልን ክፍል ቆርጦ እስከማስወገድ ድረስ የመድረስን ያህል እንደሆነ ያሳስበናል። የበደለን ወንድም ይቅርታ ማድረግ የክርስቶስን የይቅርታ ባህሪ መላበስ እንደሆነና ከተግሳፅ በፊት መነጋገር፣ ፀሎት፣ምክር ቀዳሚነት እንዳለው የወንድምን ሀጢዓት መክደንና በፍርድ ሳይሆን በይቅርታና በፍቅር መመለስ አምላካችን የእኛ እንዲሆን የሚፈልገው ማንነት እንደሆነ ያስተምራል።


ምዕራፍ 19 ከ1-12፦ ጌታ ኢየሱስ እግዚአብሔር ለክብሩ በዘፍጥረት 2፥24 ላይ በመሰረተው ጋብቻ በተባለው ተቋሙ ላይ ፈሪሳውያን ያነሱትን "ሰው በሆነው ምክንያት ሁሉ (በማንኛውም ምክንያት) ሚስቱን ሊፈታት ተፈቅዶለታልን? ለሚለው አጥማጅ ጥያቄ በሚሰጠው መልስ፦ ጌታ ሠው በደምና በስጋ ከተሳሰረበት ቤተሰቡ እስኪለያይ ድረስ እግዚአብሔር ከሰጠው ሚስቱ ጋር የነፍስ፣ የመንፈስና የአካል ጥምረት እንደሚያደርግ፣ይህም ሕብረት ከሕብረቶች ሁሉ በላጭና በአምላክ ፊትም የተቀደሰ እንደሆነ፣ ጋብቻ ለሰው ልጆች ሁሉ የተሰጠ የአምላክ ፈቃድ እንደሆነ፣ በሚልኪያስ እንደተነገረው እግዚአብሔር መፋታትን እንደሚጠላ፣ ወንድና ሴት አንድ ግዜ ከተጋቡ ይለያዩ ዘንድ መፍቀድ እግዚአብሔር ያጣመረውን በመለየት በአምላክ ስራ ውስጥ ጣልቃ የመግባት ድፍረት እንደሆነ ይናገራል። በተጨማሪም ዋናውን የስነ ፍጥረት ሕግጋትን መሰረት አድርጎም "ወንድና ሴት አደረጋቸው" በሚል ሐይለ ቃል ጋብቻ በወንድና በሴት መካከል የሚደረግ ውሕደት እንደሆነ በማስረገጥ በዘመናችን ለሚነሱ ጥያቄዎች ሳይቀር መልስ የሚሆንን ግልፅ እውነት ስለመጽሃፍ ቅዱሳዊው ጋብቻ ያስቀምጣል። ከቁጥር 15 እስከ 30 ባለው ምንባብ ውስጥ በጌታና ለኦሪት ሕግጋት ታማኝ በነበረው ሰው መካከል በተደረገው ንግግር ውስጥ ለዘመናት ፈታኝ ጥያቄ ሆነው ካሉት አንዱ የሆነውን "የእምነትነና የስራን ልዩነትና አንድነት" ጌታ ለደቀመዛሙርቱ ያብራራል። ሠው የሚድነውና የሚፀድቀው በእምነት ነው። ይህንን እውነተኛ እምነት ደግሞ በጎ ስራ ይከተለዋል። እውነተኛ እምነት በስራ እንደሚገለጽ ሁሉ እውነተኛ እምነትም በጎ ስራን ለመስራት አቅምንና ፀጋን ይሰጣል። ይህ ሀብታም ሰው የኦሪት ሕግጋትን በመጠበቅ የኖረ ነው። ማርቆስ 10፥21 ላይ "ኢየሱስም ወደ እርሱ ተመልክቶ ወደደው" የሚለው ቃል በራሱ የዚህን አይሁዳዊ ስነ ምግባር ገላጭ ሆኖ ይገኛል። ይሁን እንጂ አንድ ነገር ጎሎታል እምነት! የጌታን ግብዣ ተቀብሎ እርሱን መከተል አልመረጠም ስለዚህ በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ መዝገብ አላገኘም። ጌታን ተከትሎ ቢሆን ኖሮ ሌላ ትልቅ ደቀመዝሙር ይወጣው ይሆን ብዬ ለአፍታ እንዳስብ አርጎኛል።


በምዕራፍ 20 ከቁጥር 1 እስከ 16፦ በተወዳጁ ልዑል በጌታ የጥበብ ንግግር ውስጥ ዲናር የሚለው ቃል የደሕንነት መግለጫ ሆኖ ይነበባል። በጠዋት መጥቶ ላረሰም፣ እኩለ ቀን ላይ ለደረሰም፣ ወይንም አመሻሽ ላይ ብቅ ላለውም የእርሻው ባለቤት ሳያዳላ እኩል እንደሚከፍል በጌታችን የሚሆነው ደሕንነት እንዲሁ ነው። በእግዚአብሔርና በልጁ ላመኑ ሁሉ ደሕንነት ያለማበላለጥ የተሰጠ የፀጋ ስጦታ ነው ይለናል። ደህንነታችን በሰራነው ሰዓት ብዛት ወይንም በሰራነው ስራ መጠን የማይወሰን ክፍያውም የሚበላለጥ አይደለም ሰጭው እግዚአብሔር ነው። አንድ አይነት ደሕንነት፣ ልጅነት፣ የመንግሥቱ ወራሽነት ቢኖረንም በመንግስቱ ውስጥ በኖርንበት ዘመን በመሰጠት ባገለገልነው መጠንና ልክ ደግሞ የሽልማታችን መጠን መለያየቱን ግን ልብ ልንል ይገባል፤ ማቴዎስ 16፥27 "ያን ግዜ ለሁሉ እንደ ስራው ያስረክበዋል" ስለሚል።

24 views0 comments

Comments


Commenting has been turned off.
bottom of page