top of page
Search

የማቴዎስ ወንጌል የምንባብ ማስታወሻ፦ ምዕራፍ 21-22

Writer's picture: ወንድም አሰፋ ገብሩወንድም አሰፋ ገብሩ

በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 21 ከቁጥር 1 እስከ 11 ላይ ፀሐፊው በዘካርያስ መጽሐፍ 9፥9 ላይ የተተነበየው ትንቢት ፍፃሜ አግኝቶ ጌታ በአሕያ ውርንጭላ ላይ ተቀምጦ ወደ እየሩሳሌም እነደገባና የፍፃሜው መጀመሪያ እንደቀረበ ይነግረናል። የጌታ ተከታዮችና ሐዋርያት ልብሳቸውንና ለምለም የሆነውን ዛፍ በመቁረጥ በፊቱ እያነጠፉ ሆሳዕና ለዳዊት ልጅ እያሉ መዘመር ጀምረዋል። ፈሪሳውያንም እየሰማህ ነው ህፃናት እንኳ የማይገባህን ክብር ሲሰጡህ ባሉት ግዜ እሰማለሁ እንደናንተ ካልተገበዙ ልበ ንፁሃን ምስጋና ተዘጋጅቶልኛል ሲላቸው ይደመጣል። ከ12-17፣ ከ18-22 ከ23-41ና ከ42-46 ባሉት ክፍሎች በክርስትና እምነት ውስጥ መሰረታዊ ከሆኑት አስተምህሮዎች መካከል የተወሰኑትን ያነሳል። ከ12-17 ባለው ክፍል የፍቅር መልእክተኛ ሆኖ ለበዳዮች ይቅርታን ያስተማረን ጌታ ለዘመናት የቆሸሸውን የአባቱን ቤተ መቅደስ በቁጣ ሲያፀዳ እናነባለን። ጌታ ስለ ራሱ ክብር አልነበረም የተቆጣው ስለ አባቱ ክብር እንጂ፤ የአባቱ ቤተ መቅደስ የፀሎት ቤት መሆን ሲገባው የሌቦች ዋሻ ሆኖ ነበር። ከዚህ የምንረዳው በክርስቶስ የሆንን ሁሉ የጌታ ቤተ መቅደስ እንሆን ዘንድ በዋጋ ስለተገዛን በስጋችን (1ኛ ቆሮ. 6፥19-20) እግዚአብሔርን ልናከብር እንደሚገባ ነው። ከ18-22 ከጌታ በወጣው ሀይለ ቃል ቅጠሎችዋ ለምልመው ነገር ግን ፍሬ አልባ በነበረችው የበለስ ዛፍ ምሳሌ እግዚአብሔር በጌታ አምነን የዳን ሁሉ ፍሬያማ እንሆን ዘንድ እንደሚጠብቅብን እና ምን ያህል እምነት የእግዚአብሔርን ክንድ እንደሚያንቀሳቅስ ያስተምረናል።ከ23-41 ባለው ክፍል በሕግ መመፃደቅና ንስሀ ባለመግባት በግብዝነት ከሚኖሩት አይሁዳውያን ይልቅ ለእግዚአብሔር መገዛትን የወደዱና ንሰሀ የገቡ ቀራጮችና ጋለሞቶች የእግዚአብሔር መንግሥት ወራሾች በመሆን ሊቀድሟቸው እንደሆነ ይነግራቸዋል።ከ42-46 ባሉት ክፍሎች ጌታችን በሁላችንም ዘንድ የሚታወቀውንና ማንነቱን ገላጭ ስለሆነው "የማዕዘን ድንጋይ" ይናገራል። ማዕዘን የሚለው ቃል ዋና፣ መሪ፣ ከፍተኛ ገዥ፣ ዐናት፣ ንጉሥ የሚል ፍቺ ሲኖረው በምድር ገዥዎችና ገንቢዎች አይረባም የተባለው እርሱ የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን መንግሥት የሚቆምበት ዋንኛ መሠረት እንደሚሆነ ይናገራል።


ምዕራፍ 22፣ ከ1-14 ጌታ እንደሁልጊዜው በምሳሌ ከሰርጎች ሁሉ ስለበለጠው ሠርግ እየተናገረ ነው። እግዚአብሔር አባት ለልጁ ሠርግ ደግሷል፣ ሙሽራው ተወዳጁ ጌታ ነው፣የሠርጉ ውክልና የእግዚአብሔር መንግሥት ነው፣ የታደሙት አይሁድ ናቸው። ሊመጡ የወደዱ ሁሉ ይመጡ ዘንድ ማለፊያ ከሆነውም መዐድ ይቋደሱ ዘንድ አገልጋዮቹን አንዴ አይደለም ሁለት ግዜ ልኳል ወጥተውም ጥሪውን አድርሰዋል። የታደሙት ግን ግብዣውን ሳይቀበሉት ቀሩ (ክርስቶስን)፤ ላለመቀበል ያቀረቡት ምክንያት በደጋሹ ፊት በቂ አልነበረም (ይህ እውነተኛው መሲሕ አይደለም ሲሉ) ስለዚህ ስጦታውን የናቁትን ናቃቸው። አገልጋዮቹን ዳግም ላካቸው፦ ‘ውጡና በመንገድ የተገኙትንና ይታደሙ ዘንድ አይገባቸውም የተባሉትን ሁሉ ጥሩልኝ’ አለ (ሃጢዐተኞችና ቀራጮችን)፤ የሰርጉም አዳራሽ ሞላ። ንጉሡ ወደ ሠርጉ የታደሙትን ሊያይ ወጣ በዚያ የጥሪው ምክንያት የገባቸውና ያልገባቸው ነበሩ (የሰርግ ልብስ ያልለበሱ)። የሚገባቸው ይቀመጡ መጥፎዎች እንግዶች ግን ከሰርጉ ስፍራ ይውጡ ሲል አዘዘ። እነዚህ ሰዎች የሰርጉን ስረዐት ለመካፈል ከሰቡ ኮርማዎችና ሰንጋዎች የተዘጋጀውን ምግብ (የዘልዐለምን መንግሥት በክርስቶስ በመውረስ ከሚገኘው ሀሴትና ደስታ) መቋደስ ሳይችሉ ቀሩ። ከ15-46 ግብር ሰለመክፈል፣ ሰለትንሳኤ ሙታን ስለታላቂቱ ትዕዛዝ ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ለቀረቡለት ጥያቄ የሚሰጠውን መልስ እናነባለን፤ የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር የቄሳርንም ለቄሳር መክፈል የሚገባ እንደሆነ። በትንሣኤ ሙታን በተነሳው ጉዳይ መፅሀፍን ብታውቁስ ከትንሣኤ በኋላ በመንግስተ ሰማይ ጋብቻ የለም ሞትም አይኖርም፤ በርሱ የሚያምኑ ሁሉ እንደ መላዕክት ይሆናሉ አያገቡም አይጋቡም። አባቴ የሕያዋን አምላክ እንጂ የሙታን አምላክ አይደለም ይላቸዋል። ከ34-46 ባለው ክፍል ከትዕዛዛት ሁሉ ስለ በለጠችው ትዕዛዝ ጌታ በኦሪት ሕግ ለእስራኤል ተሰጥተው የነበሩትን 613 ሕጎች የጠቀለሉትን ሁለቱን ነገራቸው። በፍጹም የሚለውን ሀይለ ቃል ሶስት ግዜ በመጠቀም። የሚያምኑ ሁሉ እግዚአብሔርን በፍጹም ልብ፣ነፍስና ሐሳብ መውደድ ከሁሉ የቀደመው እንደሆነና ቀጣዩ ደግሞ ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ የሚሉት ናቸው።

9 views0 comments

Comments


bottom of page