top of page
Search

የማቴዎስ ወንጌል የምንባብ ማስታወሻ፦ ምዕራፍ 23-26

Writer's picture: ወንድም አሰፋ ገብሩወንድም አሰፋ ገብሩ

በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 23 ከ 1-12 ባለው ምንባብ ጌታችን ጠንከር ባሉ ኃይለ-ቃላት "በፀሎት ርዝመት እያመካኛችሁ የመበለቶችን ቤት የምትበሉ፣ ትንኝንም የምታጠሩ (ለሚጠጡት ውሃ የነበራቸውን ጥንቃቄ) ግመልንም የምትውጡ፣ግብዞችና ጻፎች፣ደንቆሮዎችና እውሮች" እያለ የአይሁድ መሪዎችን መጥፎ ምግባር ያጋልጣል። ለሕዝቡም መሪዎቻችሁ የኦሪትን ስርዓት እንደሚገባ የሚያውቁ የሚናገሩትም ሕግ ትክክል ነውና ልትታዘዙዋቸው ይገባል፤ በሙሴ ወንበር ላይ ተቀምጠዋልና። ነገር ግን በስራቸውም ሆነ በሕይወታቸውም ታማኝ ያልሆኑ፣ ለታይታ የሚኖሩ፣ ስልጣናቸውን አለአግባብ የሚጠቀሙ ስለሆኑ ስራቸውን አትከተሉ በማለት ያስጠነቅቃቸዋል። ከቁጥር 13 -39 ባለው ክፍል ጌታችን የሚናገራቸው ተግሳፆች በሙሉ ያተኮሩት በግዜው አሽንክታብ (ከቆዳ የተሰራ በውስጡ የመፅሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ያሉበት) በክንዳቸው ላይ አስረው በግብዣ ቦታዎች የክብርን ስፍራ በምኩራብም ቀዳሚውን ወንበር የሚሹ ጻፎችና ፊሪሳውያን ላይ ነበር። ቁጥር 39 ላይ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው ብላችሁ በእኔ በማመን በንሰሀ ካልተመለሳችሁ ቤታችሁ የተፈታ ሆኖ ይቀራል" ብሎ ያስጠነቅቃል።


ምዕራፍ 24 የዕብራውያን ፀሐፊ በመልዕክቱ መጀመሪያ ላይ "ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም አለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን" እንደሚል ጌታችን አዳኝ፣ ፈጣሪ የእግዚአብሔር ልጅ፣ ሊቀ ካሕን ከመሆኑ ባለፈ የአዲስ ኪዳን ነብይም መሆኑን ለማስረገጥ ሊመጣ ስላለው የመጨረሻው ዘመን ለሐዋርያቱ ይነግራቸዋል። በዚህ ምዕራፍ ጌታ በአማኞች ዘንድ በጥንቃቄ ሊወሰዱ ስለሚገባቸው የአለም መጨረሻ ምልክቶች፣ ስለ ሐሰተኞች ነቢያት፣ ‘ክርስቶስ ነን’ ስለሚሉ አሳቾች፣ ምፅዓቱን ከአብ በቀር የሚያውቅ እንደሌለና ከእርገቱ በኋላ በሮማውያን በ70 ዓመተ-ምሕረት ስለፈረሰው ቤተ መቅደስ ሳይቀር ይናገራል። በአለማችን እንደ መፅሐፍ ቅዱስ ቃል እየተፈፀሙ ያሉት አስፈሪ ነገሮች ምልክት ከመሆናቸው በተጨማሪ አሁን እኛ ባለንበት ዘመን እንኳን ሐሰተኞች ነቢያት ብቻ ሳይሆኑ የዳዊት ቤት ገዥና የመጨረሻው ነብይ ነኝ፣ በተራራ ላይ የተገለፀው ኤሊያስና የክርስቶስ ምሳሌ ነኝ፣ በቀደመው ሕይወቴ ኢየሱስ ነበርኩ ያሉና ለብዙ ንፁሃን ሰዎች ሕይወት መጥፋት ምክንያት የሆኑ ብዙ ሰዎች ተከስተዋል። ጌታ በዚህ ክፍል እየተናገረን ያለው ዘመኑን በእግዚአብሔር ቃል እንድንመረምር፣ ጌታችን ዳግም የሚመጣበት ቀን ስለማይታወቅ ንስሀ ገብተን፣ ይቅርታን ጠይቅን፣ሐሰተኞችን ለይተን፣ለፈቃዱ እየተገዛ ን ከጌታ እንዲሁ ያለ ዋጋ በተሰጠን ወደር በሌለውና ይህንን ሁሉ እንከውን ዘንድ አቅም በሚሆነን በፀጋ ስጦታው ላይ ታምን የቆምንና በመንፈሱም የተጠበቅን ሆነን እስከ ምፅአቱ ድረስ እንኖር ዘንድ አስፈላጊ ነው እያለን ነው።


ምዕራፍ 25 ከ1-13 የቆነጃጅቱን ምሳሌ፣ ከ14-30 የመክሊት ምሳሌና ከ31-46 ደግሞ ስለመጨረሻው ፍርድ ይናገራል። ሙሽራው እንደገና በታላቅ ክብር የሚመለሰው ክርስቶስ፣ አስሮቹ ቆነጃጅት ክርስቶስን ስትጠብቅ የኖረችውን ቤተ ክርስቲያንን ይወክላሉ። አምስቶቹ መብራታቸው የበራ የሚተካ ዘይትም ያላቸው ጥንቁቆችና ብልሆች፣ አምስቶቹ ደግሞ መብራታቸው የበራ ግን ሙሽራው ቢዘገይና ዘይታቸው ቢያልቅ መተኪያ ዘይት የሌላቸው ሞኞችና ዝንጉዎች ናቸው። በዚህ ስፍራ በእጅጉ አትኩሮት የሚገባው ዋንኛ ነገር ስለ ቤተክርስቲያን እየተናገረ ያለ ቢመስልም በእርግጥ የሚናገረው ምሉዕ ሰለሚያደርጓት በውስጧ ስላሉ ምዕመናን እንደሆነ ነው።አማኞች የሚኖሩት ሕይወት እንደ እግዚአብሔር መሻት ሆኖ ካልተገኘ ክርስቶስን እንደሚገባ ባላወቁና ባልተዘጋጁት ሞኞች ቆነጃጅት ላይ እንደሆነው ከጌታ መንግስት የመጉደልን ዋጋ ያስከፍላል። የራዕይን መፅሐፍ ምዕራፍ ሁለትን ስናነብ ጌታ ለአብያተ ክርስቲያናት በተናገረው መልዕክቱ ውስጥ ዕውቅና የሚሰጣቸው መልካምነቶች የመኖራቸውን ያህል የሚነቅፍባቸውም መተላለፎች አሉ (እዚህ ላይ ነቀፋዎቹን ብቻ አነሳለሁ፤ በተጨማሪም ይህ መልዕክት የተፃፈው በዚያ ዘመን ለነበሩ ቤተክርስቲያናት ብቻ ሳይሆን ዛሬም ላሉቱ እንደሆነ ልብ ልንል ይገባል)። ለምሳሌ፦ በኤፌሶን ላለችው ቤተክርስቲያንና ምእመናን "የቀደመውን ስራህን አድርግ አለዚያ እመጣብሃለሁ ንሰሀም ባትገባ መቅረዝህን ከስፍራው እወስዳለሁ"፤ በጴርጋሞን ላለች ቤተክርስቲያን "በላቅን ያስተማረ የበልዐምን ትምህርት የሚጠብቁ በዚያ ካንተ ጋር ስላሉ የምነቅፍብህ ነገር አለኝ"፤ በትያጥሮንም ላለችው "ባርያዎቼን የምታስተውን ያችን ሴሰኛዋን ኤልዛቤልን ስለምትተወት የምነቅፍብህ ነገር አለኝ"፤ በሰርዴስም ላለችዋ "ስም አለህ ሞተህማል የነቃህ ሁን"፤ በሎዶቅያ ላለችዋ "በራድም ትኩስም ስላልሆንህ ከአፌ ልተፋህ ነው" እያለ ጌታችን ይናገራል። በዚህ ምክንያት በአምላካችን ቤት ስንኖር አምላካችንን እንደ እግዚአብሔርነቱ መጠን ልናከብረው ልንገዛለት ይገባናል። በማቴዎስ 24 ቁጥር 14 ላይ ወደ ሌላ አገር የሚሄድ የሚለው ምሳሌ ወደ አባቱ ሔዶ እንደገና የሚመለሰው ክርስቶስ ለእኛ ለአማኞች በመንግሥቱ ስንኖር እናፈራበት ዘንድ የሰጠን የእኛን አቅም ግምት ውስጥ ያስገባ የመንፈስ ቅዱስን ስጦታን እና ተፈጥሮአዊ ስጦታዎቻችንን ጭምር ነው። ስጦታው አደራ ብቻ ሳይሆን የሽልማታችንም መመዘኛ ነው። የእነዚህ ስጦታዎች ምንጭ የሆነው እግዚአብሔር እንድናፈራበት ይፈልጋል በከንቱ ያለፈ ሕይወትና አገልግሎት ተጠያቂነት አለበት። ከቁጥር 31-46 ድረስ ባለው ክፍል፦ ጌታ አምላካችን ዳግመኛ ለፍርድ ይመጣል በዚያን ግዜ ሁላችንም በፊቱ እንቆማለን እንጠየቅማለን፤ የበቃ መልስ፣ የበቃ ክርስቲያናዊ ማንነትና ከሁሉ በላይ ጌታ የሰጠንን ትዕዛዛትን የጠቀለሉትን ሁለቱን ታላላቅ ትዕዛዛት ማለትም አምላክን በፍጹም ልብ፣ በፍፁም ነፍስ፣ በፍጹም አሳብ መውደድና ወንድሞችን እንደራስ መውደድ በሕይወታችን ዋንኛውን ስፍራ ሊይዙ ይገባል። ወገኖች ለካ ሐጢዓት ማለት ክፉ ማድረግ ብቻ ሳይሆን መልካሙን ሳያደርጉ መቅረትም ነው።


ምዕራፍ 26፥1-5 ጌታን የማጥፋት ሴራ እንደተጀመረ፣ ከ6-13 አንዲት ሴት ዋጋው ውድ በሆነ ሽቱ ጌታን እንደቀባችው ይህንንም ድርጊቷን ሐዋርያት የባከነ ብለው እስከ ማጉረምረም እንደደረሱ ጌታ ግን እናንተ ከኔ ይልቅ ሽቶ ተወደደባችሁ ለዚህች ሴት ደግሞ ከሽቶው ይልቅ እኔ ተወደድኩባት ስለዚህም ከዝህች ቀን ጀምሮ ወንጌሌ በሚሰበክበት ቦታ ሁሉ ይህ ያደረገችው መልካምነቷ መታሰቢያዋ ይሆንላታል ይላቸዋል። ከ14- 15 ባለው የአስቆሮቱ ይሁዳ ጌታን አሳልፎ የመስጠት ስምምነት ከ17-29 ስለጌታ እራት ይተርካል። በዘፀአት 12:43 በተፃፈው የአይሁድ ሕግ መሠረት የቂጣ በዓል ስርዓት ይከናወን የነበረው ኒሳን በተባለው (በመጋቢትና ሚያዝያ ወራት) ወር ሲሆን በአስራ አራተኛው ቀን የሚደረግና ለሰባት ቀናት እስከ 21ኛው ቀን የሚቆይ ስርዓት ነበር። የሰጠውን ስርዓት ሊፈፅም የመጣው ጌታ በዚህ ስፍራ ይሕን አደረገ። በመዐድም ቀርበው ሳለ በእንጀራውና በወይኑ ምሳሌ ስለሐጢዐት ስለሚፈሰው ደሙና ስለሚቆረሰው ስጋው ተናገረ እነሆ ዛሬም ድረስ ጌታ እንዳዘዘ ይህ ስርዐት በምዕመናን ለመታሰቢያው ይደረጋል። ቁጥር 36-46 የጌታን የፀሎት ተጋድሎን ያስነብበናል። በዘካርያስ 13:7 የተፃፈው "እረኛውን እመታለሁ የመንጋውም በጎች ይበተናሉ" የሚለው ትንቢት የሚፈፀምበት ግዜ እየቀረበ። ጌታ በሰውነቱ ሊቀበለው ያለው ስቃይ እየፈተነው፦ "ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዘነች"፣ "አባቴ ቢቻልስ ይህች ፅዋ ከእኔ ትለፍ"፣ "እነሆ ሰዓቲቱ ቀርባለች የሰው ልጅም በሀጢዐተኞች እጅ አልፎ ይሰጣል" እያለ ለእኛ የኃጢአት መሥዋዕት ሊሆን እየተዘጋጀ እንደሆነ እናነባለን። ከ47-75 የኢየሱስን መያዝ፣ በአይሁዳውያን ሸንጎ ፊት ቀርቦ ሞት እንደተፈረደበት፣ የአካል ጥቃት እያደረሱበት በመለኮትነቱ ላይ ሊዛበቱ እንደጀመሩና በመጨረሻም ጌታ እንደተናገረ የጴጥሮስን ክሕደት እናነባለን።

12 views0 comments

Comments


bottom of page