በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 27 ከቁጥር 1 እስከ 10 የይሁዳን ፍፃሜ ይተርካል። የመረጠውንና ይከተለው የነበረውን ጌታውን በሰላሳ ብር በመለወጡና ለእስራቱ ምክንያት በመሆኑ ንፁህ ደም አሳልፌ ሰጥቻለሁ በማለት በፀፀት፣ በሕሊና ወቀሳ፣ በቁጭትና በብርቱ የበዳይነት መንፈስ ሕይወቱን ጠላት። ስለዚህም ከንሰሀ ይልቅ የገዛ ራሱን ሕይወት ማጥፋት መረጠ። ከ11 እስከ 14 ኢየሱስ በጲላጦስ ፊት በቀረበበት ወቅት የተከሰሰበት ዋንኛ ወንጀል ‘የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ በማለት በእግዚአብሔር ላይ የስድብ ቃል ተናግሯል’ በሚለው ሳይሆን የአይሁድ ንጉሥ ነኝ ብሏል በሚለው ነበር። ምክንያቱም የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ማለቱ ለሮማ ገዥዎች በሞት ሊያስቀጣ የሚችል ክስ አልነበረም። የአይሁድ ንጉስ ነኝ ብሏል ከተባለ ግን ከሮም ግዛት የሚያፈነግጥ መንግሥት እመሰርታለሁ የሚል ክህደት ስለሆነ የሞት ፍርድ ያስፈርድበታል። ጲላጦስም ‘አንተ የአይሁድ ንጉስ ነህ?’ ብሎ በጠየቀው ጊዜ ጌታ ‘አንተ አልክ’ አለው። ከቁጥር 15-50 ባለው ክፍል ምንም እንኳ ጲላጦስ የጌታን ንጽህና አውቆ ብቻ ሳይሆን የሚስቱንም ጭንቀት ተረድቶ ጌታ ራሱን እንዲከላከል ቢጥርም የመጣበትን ተልዕኮ የሚያውቀው ጌታ ግን ዝምታን መረጠ። አይሁዳውያንም ከእግዚአብሔር ልጅ ከጌታ ኢየሱስ ይልቅ አመፀኛውንና ነፍሰ ገዳዩን በርባንን መረጡ። በሁለት አጣብቂኝ ውስጥ የገባው ጲላጦስም ከደሙ ንፁህ ነኝ ሲል እጆቹን ታጥቦ ጌታን ለገዳዮቹ አሳልፎ ሰጠው። ጌታ በብዙ ጉስቁልና ውስጥ ቢያልፍም ይደበድቡትና ይተፉበት ለነበሩ አመፀኞች ይቅርታን እየጠየቀ ራሱን የኃጢአት ቤዛ ለመሆን ለሞት አሳልፎ ሰጠ። በጌታ ሞት ተፈጥሮም ጭምር አዘነች፤ በምድርም ሁሉ ላይም ጨለማ ሆነ፤ የቤተ መቅደስ መጋረጃም ለሁለት ተቀደደ፤ መቃብሮች ተከፍተው ሙታኖች ተነሱ። ኢዮብ 9፥2 ‘ሰውስ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቅ መሆን እንዴት ይችላል?’ ሲል እንደጠየቀ የፅድቁንና የቅድስናውን ልክ የሚያውቀው እግዚአብሔር ደስ የሚሰኘውን መስዋዕት በክርስቶስ አደረገ። ሰው ታላቁን እግዚአብሔር በመበደሉ የከብቶችና የኮርማዎች ደም ከእንግዲህ ከኃጢአት ማንፃት አልቻሉም። ያላየነውን እግዚአብሔርን ያሳየን፣ የእርቃችን መስዋዕት የሆነልን ከዘለዓለም ሞት ወደ ዘለዓለም ሕይወት ያመጣን ጌታ እሱ ንፁህ መስዋዕት ሆነልን።
ምዕራፍ 28 ተወዳጅ ምንባብ ነው። ጌታችሁን ሰቅለን እንገለዋለን ይሞታልም አሉን። የስቃዩን ጥግ አይተናልና ፈራን። ሶስት ረጃጅም የምጥ ቀናቶችንም አሳለፍን። ጌታ ግን እነደተናገረው ሞትን ድል ነስቶ ተነሳ። ሞት ያሽንፈዋል ያሉን ሕልማቸው ሲመክን አየን። ሞቷል ያላችሁት ጌታ የታል? የዘጋችሁት የመቃብር ደጃፍስ ለምን ተከፈተ? ድንጋዩንስ ማን አንከባለለው? ከፈኑስ ይሁን አስከሬኑ ግን የታል? አልናቸው። በነሱ ብቻ አላቆምንም። ሞትን መውጊያህ የታል? ሲዖልንም ድል ማድረግህ የታል? ስንል ጠየቅናቸው መልስ ግን አልነበራቸውም። ሠይጣን አፍሯል! ኢየሱስ ግን ተነስቷል! ኢየሱስ ለፍፁም ስርየታችን መስዋዕትነት በመስቀል ላይ ከፍሎ መበስበስ ሳያውቅው አፈሩን ዘልቆ ልቆ ወጥቷል። መቃብር ውበት ካለው የጌታ መቃብር ውብ ነው። ውበቱም ባዶነቱ ነው።
Comments