የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 9 ከቁጥር 1 እስከ 38 ለትዝታ የሚሆኑ ታመን እንደነበር እንድናስታውስ የሚያደርጉ ጠባሳዎች የማይተውት የጌታ የፈውስ እጆች ስራ እየሰሩ እንደሆነ ያስተምረናል። ሽባውን፣የሞተችውን ልጅ፣አይነስውሮቹንና በአጋንንት ተይዞ የነበረውን ዲዳ ሰው እንደፈወሰ እናነባለን። በዚህ ምዕራፍ በተለየ መልኩ ለአትኩሮት የሚጋብዙ ቁልፍ ሀሳቦች፦ ቁጥር 6 ላይ የሚገኘው "በምድር ላይ ሀጢዓትን ያስተሰርይ ዘንድ ለሰው ልጅ ስልጣን አለው" የሚለውና ከቁጥር 35 እስከ 38 ያሉት ናቸው።ጌታ በነዚህ ንግግሮቹ ለማስረገጥ የፈለገው የሰው ልጅ ከዘለዓለም ሞትም ሆነ ከስጋ ህመም ለመፈወስ እምነት ያሻዋል፤ ያ እምነት በፅናት የቆመው ደግሞ በእግዚአብሔር አምላክና በላከው በልጁ በማመን ላይ ነው። እነዚህ ጎስቋሎች ወደእኔ አምነው መጡ፤ አኔም ፈውስ የልጆች እንጀራ ነውና ያንን አደረኩላቸው መተላለፋቸውንም ይቅር አልኩ ብሎ ይናገራል። በቁጥር 36 ኢየሱስ ወደዚህ ምድር መምጣት ዋነኛ ምክንያት ለሰው ልጅ ያለው ርህራሄና ፍቅር እንደሆነ እንረዳለን። የታመሙትን፣ ሀጢዓተኞች ተብለው የተገለሉትን፣ በአይሁዳውያን የተናቁትን ሂዱ አላላቸውም፤ ይልቁንስ አቀረባቸው፣ ራራላቸው። በቁጥር 38 ላይ እግዚአብሔር ከሰማይ ሆኖ ሲመለከት የሰው ልጆች በምድር ገፃት ላይ ተበትነው ነበር። የእርሻውን ዘር ይሰበስብ ዘንድ መልካምና ባለሙያ ገበሬ አልነበረም ስለዚህ የገዛ እጆቹ ማዳንን ማምጣት ነበረባቸው፤ ይህን ለማድረግ አንድያ ልጁን መላክ ነበረበት።ጌታም በዚህ ስፍራ የተልዕኮውን ጅማሬ ያበስራል። በኢሳይያስ 6፥8 ላይ "ማንን እልካለሁ?" ብሎ በጠየቀው ጊዜ "እነሆ እኔ እሄዳለሁ እኔን ላከኝ" እንዳለ በዚህ በእኛ ዘመን ጌታ ያንን እየጠየቀ ያለ ይመስላል፦ “ማን ነው እኔ አለሁ የሚለኝ?”
በምዕራፍ 10 ከቁጥር 1 እስከ 42፦ ጌታ የመረጣቸውን አስራ ሁለት ደቀመዛሙርት ለአገልግሎት እንደላካቸው ይናገራል። ጌታ ስራውን፣ለስራው የሚያስፈልገውን ሀይል፣ የስራውን ክብደትና ከስራው ጋር የሚመጣውን ፈተና የሚያውቅ ስለሆነ እንደሚገባ ሲያስታጥቃቸው እናያለን። መንግስተ ሰማያት ቀርባለች ንሰሀ ግቡ እያላችሁ ትስበኩ ዘንድ ብቻ ሳይሆን የማስተማርን፣ የመፈወስን፣ ሙታኖችን የማስነሳትንና አጋንንትን የማስወጣትን ስልጣን ሰጥቻችኋለሁ። በከንቱ ያለዋጋ የተቀበላችሁትን ያለዋጋ ስጡ። የምልካችሁ በተኩላዎች መካከል ነው፤ ስለዚህ የምታደርጉትንም፣ የምትናገሩትንም በጥበብ አድርጉ። ስለ ደህንነታችሁ እንደ እባብ ልባሞች እንደ ርግብም የዋሆች ሁኑ ይላቸዋል። ጌታችን ልቡ እየደማ የተናገረው የሐዋርያትን ፍፃሜ የሚናገረው ከቁጥር 16 እስከ 31 ያለው ክፍል ነው። የሚደርስባቸውን መከራ፣ ስደትና ሞት አስቀድሞ ያወቀ ቢሆንም በዚያ ውስጥ እሱ የፅናታቸው ምንጭና ጉልበታቸው እንደሚሆንና ተልዕኳቸውም ትርጉም አልባ እንደማይሆን፣ በሰው ፊት ለመሰከሩለት ለእነሱ በአባቱ ፊት እንደሚመሰክርላቸው የካዱትንም እንደሚክዳቸው ሲነግራቸው እናነባለን። ከቁጥር 34 እስከ 42 የጌታ ተልዕኮ በነፍስና በስጋ መካከል ሰይፍን ማምጣትና የነፍስን ጩኸት የሚያፍነውን የስጋን ስራ ማፈራረስና ነፍስን ለእግዚአብሔር ለመዋጀት ነው። ለዚህ ነው ሰላምን ለማምጣት አልመጣሁም የሚለው። ለሰው ልጅ በዚህ ምድር ታላቁና እሴት ያለው ነገር ቢኖር በክርስቶስ የዘለዓለም ሕይወትን መውረስ ነው።ለማያምኑ የጌታን ወንጌል ስንመሰክር በእኛ በኩል የሚነገረውን የሕይወት ቃል የተቀበሉትን ጌታ ይቀበላቸዋል፤ የማይቀበሉትን አይቀበላቸውም። ምን ዐይነት ሐላፊነት፣ እንዴትስ ያለ ዕዳሎት (privilege) ነው?
Commentaires