top of page
Search

የማቴዎስ ወንጌል የምንባብ ማስታወሻ፦ ከምዕራፍ 1 እስከ 2

Writer's picture: ወንድም አሰፋ ገብሩወንድም አሰፋ ገብሩ

Updated: Apr 27, 2024

የማቴዎስ ወንጌል ጸሃፊ ሐዋርያው ማቴዎስ ሲሆን ለአገልግሎት ከመጠራቱ በፊት በግብር ወይንም በቀረጥ ሰብሳቢነት ይተዳደር የነበረ አይሁዳዊ ሰው ነበር። በወቅቱ ቀረጥ ሰብሳቢዎች በአብዛኛው የአይሁድ ማኅበረሰብ የተጠሉና እንደኃጢአተኛ የሚቆጠሩም ነበሩ። ማቴዎስ ወንጌሉን የፃፈው በዋናነት ለአይሁዳውያን እንደነበር ሲታመን በሚያስተላልፈው መልዕክትና በአተራረክ ስልቱ ከማርቆስ እና ከሉቃስ ወንጌላት ጋር በእጅጉ ተመሳሳይነት አለው። በመጀመሪያው ምዕራፍ ከቁጥር 1 እስከ 17 ድረስ ስለጌታ የትውልድ ሐረግ የሚናገር ሲሆን ከቁጥር 18 እስከ 25 ድረስ የምናገኘው በነብዩ በኢሳይያስ (7፥14) ላይ እንደተተነበየው ጌታ ከድንግል በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ተፀንሶ እንደተወለደ ነው። ከአዳም በስተቀር ሰዎች ሁሉ ሰብዐዊ አባቶች ቢኖሯቸውም ክርስቶስ ግን ከማንም ምድራዊ አባት አልተወለደም። በዚህ ስፍራ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚነገረው ታላቅ የምስራች ዮሴፍ ማርያምን ሊወስድ በፈራ ግዜ የተነገረው "እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋል ስሙንም ኢየሱስ ትለዋለህ" የሚለው ነው። አጠራሩ በግሪክ ቋንቋ ሲሆን ትርጉሙም ‘ጌታ ያድናል’ ማለት ነው።

በምዕራፍ 2 ከቁጥር 1 እስከ 12 ሰብዓ ሰገል ተብለው የሚታወቁት የምስራቅ ከዋክብት ተመራማሪዎች ወደቤተልሔም ይሁዳ በኮከብ መሪነት ሊጎበኙት መምጣታቸውንና ያም በመሆኑ በነብዩ ሚክያስ (5፥2) የተነገረው ትንቢት መፈፀሙን ይነግረናል። በዚህ ስፍራ አንዱ እጅግ አስደናቂው ክንውን የሰማይና የምድር ፈጣሪና ከፍተኛ ገዢ የሆነው ጌታ በአይሁዳውያን ዝቅ ተደርገው ከሚታዩና በኑሯቸውም ድሆች ከሆኑት ወገኖች መወለዱ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ በ2ኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 8 ቁጥር 9 ላይ "የኢየሱስ ክርስቶስን ቸር ስጦታ አውቃችኋልና ሀብታም ሲሆን እናንተ በእርሱ ድህነት ባለ ጠጎች ትሆኑ ዘንድ ስለእናንተ ድሀ ሆነ"

በማለት ከቶም ሊረሳ በማይችል ውብ ቋንቋ ይህንን እውነት ይገልፀዋል። በመጀመሪያ የነበረው፣ በእግዚአብሔር ዘንድ የነበረው፣ ራሱም ፈጣሪና እግዚአብሔር የነበረው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ መሬት ወርዶ ስጋ ለበሰ፤ ከሰዎችም ጋር ኖረ፤ በበረት በጋጣ ውስጥ ከከብቶች ጋር አደረ፤ ልዑል በሞቱም ብቻ ሳይሆን በውልደቱም ለእኛ ሲል ራሱን እጅግ ዝቅ በማድረግ ታላቅ ዋጋን ከፈለ። ምዕራፍ 2 ከቁጥር 13 እስከ 23 የሚተርክልን ኢየሱስን ሄሮድስ ሊገድለው እንደፈለገና ይህም ለዮሴፍ በመልዓክ እንደተነገረው፣ ያንንም ተከትሎ ወደ ግብጽ ቤተሰቦቹና ሕፃኑ እንደ ሸሹ፣ እስከ ሄሮድስ ሞትም ድረስ በዚያ ቆይተው ወደ ናዝሬት መመለሳቸውን ነው። በትንቢተ ሆሴዕ ምዕራፍ 11 ቁጥር 1 ላይ "እስራኤል ህፃን በነበረ ግዜ ወደድሁት ልጄንም ከግብፅ ጠራሁት" ተብሎ የተጻፈውም ፍፃሜን አገኘ። ከግብፅ ስደት ከወላጆቹ ጋር ወደ ናዝሬት ከመጣ በኋላ፣ በሰላሳ ዓመቱ ገደማ እውነተኛውን የመንግስት ወንጌል ማስተማር እስከጀመረበት ጊዜም በዚያ እንደኖረ ይታመናል።

42 views0 comments

Comments


Commenting has been turned off.
bottom of page