top of page
Search

የማቴዎስ ወንጌል የምንባብ ማስታወሻ፦ ከምዕራፍ 3 እስከ 4

Writer's picture: ወንድም አሰፋ ገብሩወንድም አሰፋ ገብሩ

Updated: Apr 27, 2024

የማቴዎስ ወንጌል ከምዕራፍ 3 እስከ ምዕራፍ 4 ቁጥር 12 ድረስ ስለ ጌታ የአገልግሎት ጅማሬ የሚተርክ ሲሆን በምዕራፍ 3 ላይ ዮሐንስ መጥምቁ የጌታን መንገድ ያዘጋጅ እንደነበረም እናነባለን። ዮሐንስ ሰዎችን በዮርዳኖስ ወንዝ ውስጥ ማጥመቅ በጀመረበት ግዜ ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ለመጠመቅ እንደመጡ በክፋት፣በግብዝነት፣በተንኮልና በማስመሰል ይታወቁ ለነበሩ ለነዚህ ሰዎች ‘በኃጢአት አዝኖና ተፀፅቶ ጊዜያዊ ንስሐ ገብቶ መጠመቅ ብቻውን በቂ አይደለም ከኃጢአት ስራም መላቀቅ እንጂ፤ ያ ካልሆነ ንስሐ መግባታችሁ ምን ፋይዳ አለው? የንስሐችሁ ፍሬስ የታለ? እምነት ስራን፣ ንስሐም ከኃጢአት መመለስን ማፍራት አለበት ካላፈራ ግን ዛፉ መቆረጡ ወደ እሳትም መጣሉ አይቀሬ ነው።ይሁን እንጂ፦ እንደ እኔ ውስን ያልሆነ፣ ጫማውን እሸከም ዘንድ እንኳ የማይገባኝ ከእኔ በኋላ ይመጣል፤ እርሱ በውሀ አያጠምቅም፣ በመንፈስ ቅዱስና በእሳት እንጂ። በእውነት ንስሐ የገቡትንና ያልገቡትን ይለይ ዘንድ አዋቂ ነው፤ የውጭ ይዘታችሁን ሳይሆን የውስጥ ልባችሁን ይመረምርም ዘንድ ጠቢብ ነው" ዋ! እያለ ያስጠነቅቃቸዋል። በምዕራፍ 3 ከቁጥር 13 እስከ 17 የዮሐንስን ትህትና የተሞላ ጌታን የማጥመቅ እምቢታና ይልቁንም በጌታ እጅ የመጠመቅ መሻቱን ሲገልፅ እናነባለን። ዮሐንስ ለጌታ ማንነትና ንፅህና ከነበረው እውቀት፣ ለእርሱም ከነበረው ትልቅ ክብር የተነሳ ነበር ጌታን ማጥመቅ የተገባው እንዳልሆነ በማመን ሊከለክለው የሞከረው። ይሁን እንጂ ጌታ "አሁንስ ፍቀድልኝ ፅድቅን ሁሉ ልንፈፅም ይገባናል" ብሎ በዮርዳኖስ ወንዝ ውሃ በዮሐንስ እጅ ተጠምቋል። ተጠምቆ ከውሃው ሲወጣ እግዚአብሔር" በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው" ሲል ኢየሱስ ጌታ፣ አዳኝና መሲሕ እንደሆነ መሰከሮለታል።

ከምዕራፍ 4 ከቁጥር 1 እስከ 11 የምንማረው ኃጢአት አልባ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ በኃጢአት ሁሉ ላይ አሸናፊ እንደሆነ ለሰው

ልጅ ሁሉ ምስክር ይሆን ዘንድ ለሰው ዘር የተሰጠውን ፈተና ለመካፈል መንፈስ ወደ ምድረ በዳ እንደወሰደውና በዚያ እንደተራበ፣

እንደተጠማ፣ ፈታኝም መጥቶ እንደ ፈተነውና በኃጢአት እንዲወድቅ እንደተገዳደረው ነው። ነገር ግን ጌታችን ፍፁም አምላክ ፍፁምም ሰው ስለነበር በፈተናው አልተሸነፈም። ለአርባ ቀናት ምግብ ስላልበላ በመጎምዠት ፈተነው "ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል እንጂ በእህል ብቻ አይኖርም" ሲልም ገሰፀው። የእግዘብሔር ልጅነቱን ይጠራጠር ዘንድ ራሱን ማዳን በመቻሉና ባለመቻሉ ተገዳደረው "ጌታ አምላክህን አትፈታተነው ተብሎ ተፅፏል" አለው። ይሄ የሰይጣን የፈተና ጥያቄ በጌታ የስቅለት ግዜም ተነስቷል (ማቴዎስ 27፥40)። ለሶስተኛ ግዜም ሰይጣን የጌታን የፍጥረት ሁሉ ባለቤት እንደሆነ እያወቀ የአለምን ስልጣንና ክብር በማሳየት ፈተነው። ኢየሱስም " ለጌታህ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ ተብሎ ተፅፏል" አለው። በነዚህሕ ፈተናዎች ውስጥ በጉልህ የተጠቀሱት የሰይጣን ሙከራዎች አንደኛ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን እንዲጠራጠር ማድረግ። ሁለተኛ ጌታ የገዛ ሀይሉን ለራሱ ምቾትና ፍላጎት ይጠቀምበት ዘንድ መገፋፋት።ሶስተኛ እንደ ጤዛ ታይቶ ከሚያልፈው ጠፊ አለምና በውስጧም ካለው ከንቱነት ጋር ፍቅር ወድቆ የመጣበት ታላቁ ተልዕኮው እንዲጨናገፍ ማድረግ ነበር። ልብ ልንለው የሚገባው ነገር ጌታ በነዚህ ሁሉ ፈተናዎች ሰይጣንን የሞገተው የእግዚአብሔርን ቃል በመጥቀስ እንደሆነ ነው። እኛ የምንፈተነውን ፈተና ሁሉ ተፈትኗል፤ ፀንቶ መቆም እንዴት እንደሚቻልም ምሳሌ ሆኖናል።

ምዕራፍ 4 ከቁጥር 12 እስከ 25 ላይ ደግሞ ጌታ አገልግሎት መጀመሩን ያበስረናል። የጌታ አገልግሎት የተጀመረው በገሊላ ሲሆን

በኢሳይያስ 9 ከቁጥር 1 እስከ 2 የተነገረው ትንቢት ፍፃሜ እንዳገኘና ጌታ መንግስተ ሰማያት (የእግዚአብሔር መንግሥት) ቀርባለችና ንስሀ ግቡ" የሚለው ቃሉና የጌታ የመጀመሪያው ስብከት የመጣበት ተልዕኮ መሠረትና ምሰሶ እንደሆነ እንረዳለን። ከዚህ የምንማረው ኢየሱስ ራሱ ወደዚህ ምድር የመጣ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደሆነ ነው። ምዕራፍ 4 ከቁጥር 18 እስከ 25፦ የመጀመሪያዎቹ የክርስቶስ ደቀመዛሙርትን ስምዖንና እንድርያስ በኋላም ያዕቆብና ዮሐንስን ‘ኑ ተከተሉኝ፤ ከእንግዲህ አሳ አታጠምዱም ይልቁንስ ለመንግስቴ የሚሆኑ ሰዎችን ታጠምዳላችሁ’ እንዳላቸው እናነባለን። ከመታዘዛቸው የምንማረው ጌታን ለመከተል መወሰን ማለት በሕይወታችን ዋጋው ብዙ ነው የምንለውን ነገራችንን ሁሉ መጣል እንደሆነ ነው።


33 views0 comments

Comments


Commenting has been turned off.
bottom of page