top of page
Search

ጥቂት ማስታወሻዎች ከሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ

Writer's picture: ወንድም አሰፋ ገብሩወንድም አሰፋ ገብሩ

የሐዋርያት ሥራ መፅሐፍ ያላለቀ መፅሐፍ ነው። ጌታችን ዳግም በታላቅ ክብር እስኪመጣ ድረስ መንፈስ ቅዱስ ለእኛ ከተሰጠበት ከበዓ ለሐምሳ ቀን ጀምሮ እየሰራ ነው። ለዚህም ነው ያላለቀው ወይም ያልተደመደመው መፅሐፍ ተብሎ በቁልምጫ የሚጠራው። ሁላችንም አማኞች እየፃፍን ነው። ወንድሜ የራሱን የሐዋርያት ስራ መፅሐፍ እየፃፈ ነው፤ እሕቴም የራሷን መፅሐፍ እየፃፈች ነው። እኔም ራሴ የራሴን መፅሐፍ እየፃፍኩ ነው።እኛ ከአራቱ ወንጌላት ቀጥሎ አምስተኛው ወንጌሎች ነን ጥያቄው ለመፃኢው ትውልድ የምንተወው የእኛ የግላችን የሐዋርያት ስራ መፅሐፍ ይዘት ምንድነው ነው? የዚህ መፅሐፍ ፀሐፊ ከወንጌላት አንዱ የሆነውን የሉቃስን ወንጌል የፃፈልን የተወደደው ሐኪም ወንጌላዊው ሉቃስ ነው። ይህ መፅሐፍ የተፃፈው ከጌታ ልደት በኋላ ከ60 እስከ 65 ዓ.ም በነበሩት አመታት ሲሆን ተደራሽነቱ ልክ አንደ ወንጌሉ ቴዎፍሎስ በመባል ይታወቅ ለነበረው የሮማ መንግሥት ከፍተኛ ባለስልጣን እንደሆነ ለሚታመን ሰው ነው። ይህ ግዜ ጳውሎስ በሮም በቁም እስር የነበረበትና እርሱ በሰበከው በዚህ የክርሰቶስ ወንጌል ላይ ጥያቄዎች የተነሱበት ስለነበር ሉቃስ ጌታችን ኢየሱስ ማን ነው? ክርስትናስ ምንድን ነው? ለሚለው ጥያቄ መልስ ለመስጠት የፃፈው መልዕክት ነው። የሐዋርያት ሥራ (በቅጥያ ስሙ የመንፈስ ቅዱስ ሥራ) ሥነ ፅሁፋዊ ውበቱ አስገራሚ ከመሆን ባለፈ የተፃፈበትን አላማ በትክክል ያደረሰ፣ የመንፈስ ቅዱስን ስራ የገለጠና ክርስትናን ከጥፋት የተከላከለ እጅግ ጉልበታም መፅሐፍ ነው። ሉቃስ ለቴዎፍሎስም ለእኛም የፃፈውን ይሕንን መፅሐፍ የሚጀምረው ወንጌሉን ፅፎ ካቆመበት ከኢየሱስ እርገት ሲሆን ተወዳጁ ጌታ ሞትን ድል ነስቶ መነሳት ብቻ ሳይሆን ሕያውም ሆኖ በሐዋርያት መካከል ለአርባ ቀናት እንደቆየና የሰበከው ወንጌልና ስራ እንዲቀጥልና ይሕንንም ስራ ወደ ፍፃሜ ለማድረስ ይችሉ ዘንድ በዮሐንስ ወንጌል እንደተማርነው ሐዋርያት በመንፈስ ቅዱስ እንደሚጠመቁ ቃል ኪዳን የገባላቸው መሆኑን በመግለፅ ነው። ታድያ ይህ የክርስትና እምነት እውነት ለመሆኑ ከሞት የተነሳው ኢየሱስ የሰበከው ወንጌል ከሞት በፊት የነበረው ኢየሱስ ከሰበከው ወንጌል ጋር አንድ ከመሆኑ የበለጠ ምን የተሻለ ማስረጃ ማቅረብ ያስፈልጋል? ሌላው የዚህ ምዕራፍ አስደናቂ ክንውን በፍርሃት ለተሞሉት፣በራቸውን ዘግተው በጭንቅ ለተቀመጡት የሰጣቸውን ወንጌልና ተስፋ ለተጠራጠሩት ሐዋርያት ራሱን ያለ ምስክር የማይተወው ክርስቶስ ከትንሳኤ በኋላ በተዘጋ ቤት ውስጥ ለሰው አእምሮ እጅግ አስደናቂ በሆነ መልኩ መገለጡ ብቻ ሳይሆን ከሐዋርያት ቀጥሎ በቁጥር ከአምስት መቶ በላይ ለሚሆኑ ሌሎች ሰዎችም ጭምር መታየቱ መቻሉ ነው። ሉቃስ የጌታ ክርስቶስ ወደምድር የወረደበት ስራና ተልዕኮ በድል መጠናቀቁን ሲገልጽ "እነርሱ እያዩት ከፍ ከፍ አለ ደመና ከዓይናቸው ሠውራ ተቀበለችው" ይለናል። ይሕ ክስተት የጌታን አምላካዊ ስልጣን የገለጠ፣ ከፍጥረት ሕግም በላይ መሆኑን ያሳየ፣ ወደላይ መሄዱንና በቀደመውም ክብሩ በአብ ቀኝ መቀመጡን የመሰከረ ነው። ከታላቁ የእግዚአብሔር መንፈስ ጋር ያዋደደን ተወዳጅ ምዕራፍ! በዚሁ መፅሐፍ ምዕራፍ ሁለት ላይ የምንከተለው ወንጌል ምሰሶዎች ከሆኑት የእምነት አስተምህሮዎች መካከል ከዋንኞቹ አንዱ የሆነው ጌታችን በገባዉ ቃልኪዳን መሠረት እርሱ ወደ አባቱ ከሄደ በኋላ በእርሱ ምትክ ወደ እውነት ሁሉ እየመራ በተቀደሰ ሕይወት እንኖር ዘንድ የሚያግዘን ቅዱሱ መንፈስ በሐዋርያት ላይ መውረዱ ነው። ይሕ መንፈስ ቅዱስ የወረደበት ቀን የዋለው ከኢየሱስ ትንሣኤ በኋላ በሃምሳኛው ቀን ስለነበር የቃሉ ፍች ከግሪክ ቋንቋ ተወስዶ ጴንጤቆስጤ ወይንም በዓለሀምሳ ተባለ። ሌላው አስገራሚው ነገር በግልፅ ግንኙነቱን ለማስቀመጥ ትንሽ አዳጋች ቢሆንም ይህ የበዓለሀምሳ ቀን ከዚህ ቀደም በዘፀአት 34፥22 ና በዘዳግም 16 ከ9-10 የእግዚአብሔር ሕግ ለአይሁድ የተሰጠበት ቀን፣ በዘዳግም 16፥10 የሰባቱ ሱባኤ በዓል፣በዘፀአት 23፥16 የመከር በዓል በዘሁልቁ 28፥26 የበኩራት ቀን ብለው የሚያከብሩት ቀን መሆኑም ጭምር ነው። ከዚህ ታላቅ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት በኋላ የሐዋርያት ኑሮ ሕይወትና አገልግሎት አስገራሚ ለውጥን አሳይቷል። ከሞት የተነሳው የክርስቶስ ሐይል በሕይወታችው ከማደሩ የተነሳ የማይናወጥ ፅኑ የእምነት መሠረት እንዲኖራቸው፣የሞት ፍርሃትና ጥርጣሬያቸው እንዲወገድ ሕይወታቸው በመንፈስ ቅዱስ ቁጥጥር ስር እንዲሆንና ስለ ወንጌል ያለ ስጋት በዚህ ሀይል እገዛ መናገር ይችሉ ዘንድ ቃላቸውም የእግዚአብሔር ቃል እንዲሆን አቅም ሆኗቸው መገኘቱ ነው። በዚህ ወቅት ከተከናወኑትና የመንፈሱን እውነተኛነት ካስረገጡት ኩነቶች መካከል በዘፀአት 3፥2 ለሙሴ የእግዚአብሔርን ሀልዎት የገለፀው እሳትና በሕዝቅኤል 37፥9 ለሙታን ሕይወትን የሰጠው የእግዚአብሔር ሀይል መገለጫ የሆነው ንፋስ መጠቀሳቸው ብቻ ሳይሆን በዓሉን ለማክበር ከተለያዩ ቦታዎች የተሰበሰቡት ሰዎች መስማት በሚችሉባቸው ቋንቋዎች (2፥9-12 መነበብ ከተቻለ ድንቅ ይሆናል) ሐዋርያት መናገር መቻላቸው ነው። በመጠራጠሩ ዕውቅና የነበረው ሐዋርያው ጴጥሮስ ሳይቀር ሁሉንም ሐዋርያት ወክሎ የኢዮኤልን መፅሐፍ መሰረት በማድረግ የተናገራቸው ሐይለ ቃሎች፣ ዐይነስውሩን ለማኝ የፈወሰበት የመንፈስ ቅዱስ የፈውስ ስጦታ ሦስት ሺህ ሰዎችን ወደ እውነተኛው እምነት ያመጣው ስብከቱ፣ ከዮሐንስ ጋር ትከሻ ለትከሻ ቆሞ በአይሁድ ሸንጎ ፊት ክርስቶስን፣መንፈስ ቅዱስንና የጌታን ወንጌል እውነተኛነት የሞገተበትና አይሁድ በአስፈራሩት ወቅት "እኛስ ያየነውንና የሰማነውን ከመናገር ወደኋላ አንልም" በማለት በፅናት መቆሙ የዚሕን ታላቅ መንፈስ ማንነት፣ ሐይልና እውነተኝነት የገለፀ ነው። ምዕራፍ 15 የኢየሩሳሌም ጉባዔ። ጉባኤው የተካሄደው ከጌታችን ልደት በኋላ ከ48-50 ዓ.ም በኢየሩሳሌም ከተማ ሲሆን ሁሉም ሐዋርያት የተካፈሉበት ነበር ተብሎ ይገመታል።በዚህ ምዕራፍ በተለምዶ የኢየሩሳሌም ጉባኤ ብለን በምናውቀው ጉባዔ ላይ ሉቃስ በቤተክርስቲያን ላይ ተነስተው ከነበሩት ፈተናዎች እጅግ አጠያያቂ የነበረውን ጉዳይ ጴጥሮስና ያዕቆብ እንዴት ባለ ጥበብና መገለጥ በመናገር መስመር እንዳስያዙት ያስረዳናል። ከአይሁድ እምነት የመጡ ክርስቲያኖች ከይሁዳ ወደ አንጾኪያ በመሔድ በጌታ ወንጌል አምነው ወደ ክርስትና የመጡ አረማውያን ወንጌልን ከመቀበላቸው በፊት በብዙ እርኩሰት ውስጥ ስለነበሩ ያንን ልምድና መተላለፍና ይዘው ወደ ቤተ ክርስቲያን ይመጣሉ ከሚለው ስጋት የተነሳ ይሕንን ለማጥራት ከወንጌል በፊት በነበረው የአይሁድ ሕግ ስርዓት በማለፍ ከአይሁድ ሕጎች አንዱ የሆነውን የግርዘት ስርዓት መፈፀም አለባችሁ ይሕንን ስርዓትና ሕግ ካልፈፀማችሁ ልትድኑ አትችሉም በማለት ሐሰት የሆነ ወንጌል ማስተማር በመጀመራቸው ቤተ ክርስቲያንና አማኞች ነውጥ ውስጥ እንዲገቡ ምክንያት ሆኑ (ይሕ ትምህርት እነዚህን አማኞች ብቻ ሳይሆን ጴጥሮስን ሳይቀር በወንጌል ከአመኑ አረማውያን ጋር ሕብረት ማድረጉንና መዐድ መቋደሱን እስኪያቆም ድረስ የተገዳደረ ትምህርት የነበር ብቻ ሳይሆን በገላትያ ምዕራፍ ሁለት ላይ ጳውሎስ በቁጣ ጴጥሮስን "አንተ አይሁዳዊ ነህ ሆኖም በአህዛብ ስርዐት እንጂ በአይሁድ ስርዐት አትኖርም ታድያ አሕዛብ የአይሁድነ ስርዐት እንዲከተሉ እንዴት ታሳድዳቸዋለህ ሕግን በመጠበቅ ማንም አይፀድቅም" ብሎ በቁጣ ይገስፀው ዘንድ ምክንያት የሆነ ትምህርትም ጭምር ነበር) በዚህ ምክንያት ጳውሎስና በርናባስ ወደ እየሩሳሌም በመሔድ በዚህ ጉባኤ ከሐዋርያት ጋርም እንዲመክሩ ሆነ ይሕም በታሪክ ውስጥ የኢየሩሳሌም ጉባኤ በመባል ይታወቃል። በዚሕ ጉባኤ በሕግና በጌታ ፀጋ መካከል ያለውን ልዩነት፣የፀጋን ልቀትና ከሕግም በላይ ማራመድ ማስቻሉንና የኦሪት ሕጎችን ከወንጌል ጋር መቀላቀል ሊያመጣ ስላለው አደጋም ምክክር የተደረገበት ጉባኤ ነበር። ጴጥሮስም በመጨረሻ ከጳውሎስ ጋር ስምም በመሆን "አባቶቻችንም እኛም ያልቻልነውን ቀንበር የነበረውን የኦሪት ሕግ ዳግም በእኛ ላይ ለመጫን ለምን ትፈትኑና ላችሁ እኛ እራሳችን የዳንነው እንደ አረማውያን በጌታ ኢየሱስ ፀጋ ነው እንኪያስ እኛ አይሁዳውያን ሕግን ፈፅመን መዳን ካልሆነልን ለአረማውያንማ እንዴት የከፋ አይሆንባቸውም በማለት ሞግቷቸዋል። ሐዋርያው ያዕቆብም ስምዖን እንዳለው በሚል መነሻ ሐሳብ የነቢዩ የአሞጽን ትንቢት መሠረት አድርጎ ወደ እግዚአብሔር የተመለሱትን ሰዎች እንዳናስቸግራቸው ልንጠነቀቅ ይገባል በማለት ለጉዳዩ የጠራ መቋጫ ሰጥቶበታል። ከዚሕ ምዕራፍ በኋላ ባሉት አስራ ሶስት ምዕራፎች ሉቃስ በአዲስ ኪዳን አስራ ሶስት መፃህፍትን (ዕብራውያንን ሳይጨምር) ያበረከተልንን የወንጌል አርበኛና ታላቅ ተዋጊ፣ ሐዋርያ መምህርና ሰባኪ፣ የእግዚአብሔርን እውነተኛ አገልጋይና መሪ በመሆን እስከ ሞቱ ድረስ ታማኝ የነበረውን ጳውሎስን ከእርሱ ቀድሞ በጥልቀት ከእኛ ከአማኞች ጋር ያስተዋወቀባቸው ምዕራፋት በመሆናቸው በጳውሎስ መልዕክቶች ውስጥ ልንመለከታቸው እንችላለን።

14 views0 comments

Коментарі


bottom of page