top of page
Search

የማቴዎስ ወንጌል የምንባብ ማስታወሻ፦ ምዕራፍ 14-16

በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 14 የኢየሱስን ታላቅነት ለሕዝብ ሁሉ በአደባባይ እየመሰከረ መንገድ የጠረገው ቀዳማዊው የጌታ ወዳጅ ዮሐንስ መሰዋቱን፣ ጌታ ከአምስት ሺህ ሰዎች በላይ በሁለት አሳና በአምስት እንጀራ መመገቡን፣ ደቀመዛሙርቱ የተኙባት ጀልባ በማዕበል በተናወጠች ግዜ ኢየሱስ ሊታደጋቸው በውሀ ላይ እየተራመደ መምጣቱን እናነባለን። የጌታ ወዳጅ ዮሐንስ አሟሟት እጅግ የከፋ እንደነበር የሰማው ጌታ ምንም እንኳን ሞት የሰው ልጅ እጣ ፈንታ እንደሆነ ቢያውቅምና ቅዱሱ መፅሐፍ የሚለን ነገር ባይኖርም በጥልቅ እንዳዘነ መገመት አያዳግትም። ከቁጥር 13 እስከ 21 ስናነብ፦ ሐዘንም በጉዞም የደከመው ጌታ በታንኳ ወደ ምድረ በዳ ፈቀቅ ባለበት ጊዜ (በሄሮድስ እየተፈለገም እንደሆነ ልብ ይሏል) ተከትለውት የመጡትን 5 ሺህ ሰዎች ድካምና መራባቸውን አይቶ እንደራራ የተገኘውን አሳና እንጀራ ከአብ ጋር ባርኮ እንደሰጣቸው ተመግበውም ብዙ እንደተረፈ እናነባለን። ደቀመዛሙርቱ ሰው ብዙ መዐዱም ትንሽ ነው ቢሉም ማብዛት ገንዘቡ የሆነው አምላክ በእምነት ወደ እርሱ ለመጡ የተረፈ መዐድ ከፈውስ ጋር እንዳዘጋጀላቸው እናያለን። መፅሐፍ በመዝሙር 136:25 ላይ “ለስጋ ሁሉ ምግብን የሚሰጥ የሰማይ አምላክን አመስግኑ” እንዲል።


ምዕራፍ 15፥1-9 የፈሪሳውያን መሪዎች የብሉይ ሕግ፣ ወግና ባሕላቸውን መነሻ አድርገው የደቀመዛሙርቱን ሳይታጠቡ መመገብ ባነሱ ጊዜ ውጫዊ አካላቸውን የሚያነፁ ልባቸው ግን በግብዝነትና በትዕቢት የቆሸሸ ለነበረው ፈሪሳውያን "በአልታጠበ እጅ መብላት ሰውን አያረክስም። እናንተ አባትና እናትህን አክብር ለሚለው (ዘፀአት 21፥7) ሕግ ላለመገዛት በእግዚአብሔር ላይ እያመካኛችሁ አባትና እናታችሁን አትረዱም እነዚህን እጃቸው ቢቆሽሽም ልባቸው ንፁህ የሆነውን ግን ልትወቅሱ ትሞክራላችሁ ይላቸዋል።በዚያን ግዜ አይሁዳውያን ለእግዚአብሔር የተለየ ስጦታ (ኮርባን) ብለው የሚያስቀምጡት የስለት ገንዘብ ነበራቸው ይህን ስለት እስኪሞቱ ድረስ ጠብቀው መስጠት ስለሚችሉ ወላጆቻቸው በሚጠይቋቸው ግዜ ለእግዚአብሔር የተቀመጠ ነው በሚል ሽፋን (ቁጥር 6) አይረዷቸው ስለነበር ጌታ ይህንን ግብዝነታቸውን በዚህ ስፍራ በገሀድ ያጋልጣል። ከቁጥር 10 እስከ 39 ድረስ ፀሀፊው ጌታ ያደረጋቸውን እጅግ ድንቅ ተዓምራቶችን ቢናገርም የበለጠ ያተኮረው ግን በዚህ በእኛ ዘመን እንኳን ሳይቀር ከመብል ጋር በተያያዘ ለሚነሳው ሙግት ጌታ መልስ የሰጠበትን ጥቅስ ነው። የምግብ እርኩሰት የለውም የማይስማማ እንጂ ይለናል፤ ለጤናችን እስከተስማማ ድረስ ብንመገብ ጉዳትም ሀጢዐትም የለውም የከፋውስ ልባችንን መሰረት አድርጎ በአፍ የሚወጣው አፍራሽ ንግግር እርሱ ተናጋሪውንም ሰሚውንም ያረክሳሉ በእግዚአብሔርም ዘንድ ፀያፍ ነው ይላል። ወደ አፋችን የሚገባውን እንዳይጎዳን መርጠንና አጣፍጠን እንደምንመገብ ሁሉ ከአፋችን የሚወጣው ቃል እንዲሁ የሚያንፅ ፣የማያረክስና የተመረጠ ሊሆን እንደሚገባ ሲያስተምር።


በምዕራፍ 16 ከቁጥር 1 እስከ 12፦ በሚታይ ነገር ላይ የተመሠረተ እምነት ለነበራቸው ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ማየትስ ብትችሉ ከሰማይ ቅላት የበለጠ ምልክት በመካከላቸሁ አለ። አዲስን ምልክት ለምን ትሻላችሁ? ምልክት የሚበቃ ከሆነ በመካከላቸሁ ያደረኩትን ብዙና ከበቂም በላይ ነበር። እናንተ ግን ልበ ደንዳኖች ስለሆናችሁ ዛሬም ምልክትን ትጠይቃላችሁ ይላቸውና በርሱ ላመኑበት ደግሞ ልባችሁን ከተጠራበት ቃል ኪዳን ይፋታ ዘንድ በሀሰት ትምህርት ለእምነት አመንዝራነት ከሚጋብዙ ከእንደዚህ አይነቶቹ ፈታኞች ተጠንቀቁ ይላቸዋል። ከቁጥር 14 እስከ 20 ድረስ የደቀመዛሙርቱን እምነት ፅናት ለማስረገጥ "እኔን ማን ትሉኛላችሁ" በማለት ጌታችን የክርስትና መሰረት የሆነውን ግዙፍ ጥያቄ ይጠይቃል። ለተጠራበት የክርስቶስ መንግሥት ወንጌል ሲዋደቅ ተዘቅዝቆ በመስቀል ተሰቅሎ እስከ መሞት ድረስ ታማኝ በመሆን ተልዕኮውን የፈፀመው ጴጥሮስ "አንተ ክርስቶስ የህያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ" ብሎ በመመስከሩ ጌታ በብዙ በረከትና ስልጣን ባርኮታል (ቁጥር 18-19)። ከቁ 21 እስከ 28 ከላይ ባሉት ጥቅሶች ውስጥ በብዙ የተባረከው ጴጥሮስ በዚህ ስፍራ ጌታን በተከላከለው ግዜ ጌታ ሲገስፀው እናነባለን።ይሄ ጠቢብ ጌታ የተከታዮቹን ድካም አይደብቅም ብርታታቸውን ሳይሸልም አይተውም።

38 views0 comments

Comments


bottom of page