የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 5 መጀመሪያ እስከ ምዕራፍ 7 መጨረሻ የምናገኘው “የተራራው ስብከት” በመባል የሚታወቀውን የጌታን ትምህርት ነው። በምድራችን ላይ ብዙ ታላላቅ ተናጋሪዎች ተነስተው ተናግረው አልፈዋል። ለምሳሌም፦The World's Great Speeches በሚል ርዕስ የተፃፈውንና 278 ንግግሮች ያሉበትን መፅሐፍ መጥቀስ ይቻላል። ንግግሮቻቸው በታሪክ ተመዝግቧል፤ ይሁን እንጂ ከተናገሩት ንግግር ጋር የሚዛመድ ክስተት በምድራችን ላይ ካልመጣ በስተቀር ማንም አያስታውሳቸውም። ከአለም እጅግ ብዙው ሕዝብም አያውቃቸውም።ጌታችን የሰበከው ስብከት ግን ግዑዛን የሆኑት ሰማይና ምድር ሳይቀር የሰሙት፣ ካለፈ ጊዜ ጋር ያላለፈ፣ እኩያና የሚተካከለው ያልተገኘለት፣ በእግዚአብሔር መንፈስ ሆነው ለሚሰሙና ለሚያነቡት ሁሉ እውቀትና የቋንቋ ባለቤት መሆንን የማይጠይቅ ነገር ግን የሚያንፅና የሚያርቅ፣ የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ እንዴት እንደሚቻል ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ከራሱ በእግዚአብሔር አንደበት የተነገረ ሕያው ቃል ነው።
ከምዕራፍ 5 መጀመሪያ እስከ ቁጥር 12፣ ጌታ ስለ ብፅዕና ከተናገራቸው ሃሳቦች ከምንማራቸው ውስጥ የሚከተሉትን መጥቀስ
ይቻላል።
እግዚአብሔርን አንተ ብቻ የሙላቴ መለኪያ ነህ ብሎ ከትምክህት ነፃ ሆኖ በመንፈስ ድሀ መሆን የሚያስገኘው ብፅዕናን፤ እንዲሁም በመተላለፋችንና በሀጢዓታችን በመፀፀት እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በሆነ ሀዘንና ንስሀ የምናገኘው መፅናናትን።
ማቴዎስ 11፥29 ላይ ጌታ ‘እኔ የዋህና ትሁት ነኝ ከእኔ ተማሩ እንዳለ’ በመንፈስ ቅዱስ የሆነ የዋህነት ያለው አማኝ የራሱን መብት በዕውቀት የጣለ፣ስለራሱ ክብር ግድ ሳይኖረው ወንድሜ ከእኔ ይሻላል ያለ፣ ለተበደለው በደል ከበቀል ይልቅ ይቅርታን የመረጠ እርሱ የእግዚአብሔር መንግስት ወራሽ እንደሆነ (2ኛ ቆሮንቶስ 6፥10)።
የአምላኩን ፅድቅ በመራብ፣ በእግዚአብሔር ህልውና ውስጥ ሁሌም ለመኖር በመጠማት፣ ከራሱ ደስታ ይልቅ የአምላኩን ደስታ በማስበለጥ፣ ለፅድቅ እሺ ለሀጢዓት እንቢታን የመረጠ እርሱ እግዚአብሔር ጥጋቡ እንደሚሆንለት።
ምሕረትን ማድረግ ለመማር መጀመሪያ ምሕረትን መጠየቅ፣ የተማረና ብዙ የተተወለት ደግሞ የሚምርና የሚተው እንደሚሆን ይህም ምሕረት በምህረት ስራ እንደሚገለጥ።
እርቅና ሰላም የእግዚአብሔር ሐብት እንደሆነ አውቆ በሰላምና በፍቅር የሚኖር ከፀብ ይልቅ የሰላምና የእርቅ ዘር የሚዘራ እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ ተብሎ እንዲጠራ እዳሎት እንዳለው ።
በምዕራፍ 5 ከቁጥር 13 እስከ 16፦ አለምና ስጋ አንድ ናቸው ሁለቱም በመበስበስና በመሽተት ይታወቃሉ ። ጨው ግን እንዳይበላሽና እንዳይበሰብስ ይጠብቃል። የዚህች አለም ያልተበላሸና መልካም ነገሯ እናንተ ተከታዮቼ ናችሁ። የዚህች አለም ሀጢዓንና አለመጣፈጥን እግዚአብሔር ገሀድ የሚያወጣውና የሚገልጸው በእናንተ ብርሐንነት ነው። ስለዚህ የዚህን አለም አለመጣፈጥ ጣዕም ያለው ለማድረግ፣ በጌታ መንፈሳዊ ጨውና ብርሃን ትሆኑ ዘንድ ተጠርታችኋልና በኑሮአችሁና በስራችሁ ለአምላካችሁ የክብሩ ምክንያት ሁኑ እያለን ነው።
ከምዕራፍ 5፥17 እስከ 7፥29፦ ጌታ ኢየሱስ ሕግንና በነቢያት የተነገረውን ትንቢት ሊፈፅም እንጂ ሕግን ለመሻር አለመምጣቱን ለማስረገጥ የተጠቀመበት ሀይለ ቃል "ሰማይና ምድር እስኪያልፍ ድረስ ከሕግ አንዲት የውጣ ወይንም አንዲት ነጥብ ከቶ አታልፍም" የሚለው ሲሆን በዚህ ጌታ ለሕግ ሁሉ በመታዘዝ ሊገኝ ስለሚችለው የእግዚአብሔር በረከት ያስተምረናል። አትግደል የሚለውን በወንድም ላይ ከመቆጣት፣ከአልታረቀ አንደበት በሚወጡ ቃላቶች ሌላውን ወገን ማቁሰልን ከገሐነም እሳት ፍርድ ጋር፣ በአካል ሀጢዐትን መፈፀም ብቻ አይደለም ተመልክቶ መመኘትን ከአመዝራነት ጋር፣ በመበደል ምክንያት ከሚፈፀም በቀል ይልቅ መመረቅን፣ይቅርታንና በጎነትን መምረጥ እግዚአብሔር ወደሚሻው ፍጽምና የሚያቀረብ እንደሆነ እየተናገረ ሕግን የበለጠ ጥብቅ ያደርገዋል። ጌታ ሕግጋትን ሁሉ ቢያጠብቃቸው ለመፈፀምም ከባድ ቢመስሉ ከሕግ ጋር ሲወዳደር አቅም የሚሆን ልቀት ያለው ከተራው ሰው ማንነት ይልቅ የበለጠ ማንነት የሚያላብስ “ፀጋ” የተባለ የሚያግዝ ስጦታ እንካችሁ ብሎ በነፃ ችሮናል።
በምዕራፍ 6 ባሉት 34 ምዕራፎች በክርስቲያናዊ ስነ ምግባሮች በማተኮር ጌታ ለታይታ የሚደረጉ ማናቸውም ነገሮች በእግዚአብሔር ፊት እንዴት ፀያፍ እንደሆኑ ነው የሚያስተምረን። ምንም አይነት ስራ ብንሰራ አምላካችን የሚመለከተው ስራውን ሳይሆን ለመስራት የተነሳንበትን አላማ ወይንም ምክንያት ነው።ውጤቱ ለራስ ዝናና ክብር እንጂ ለእግዚአብሔር አይደለምና በሰማይ መዝገብ ለመሰብሰብ አይሆንም ስለዚህ ለድሆች ስንሰጥ፣ ስንፀልይና ስንፆም በፍፁም ያንን እያደረግን እንዳለን ይታወቅ ዘንድ አለማስፈለጉን ነው። ስንሰጥ ቀኛችን የሚያደርገውን ግራችን እስካያውቅ ድረስ፤ ስንፀልይ ዛሬ ዛሬ እየተዘነጋ ያለውን ጌታ ያስተማረንን ታላቁን ፀሎት መሰረት አድርገን ለታይታ በአደባባይ እንዳይሆን፤ ስንፆም እንደ አይሁድ ከሰዎች ዘንድ የምስጋና ምንጭ
እንዲሆንልን ሳይሆን በእግዚአብሔር ፊት በትህትናና ንስሀ የምንገባበት፣ ምስጋና የምናቀርብበት መንፈሳዊ ድርጊት መሆኑን አውቀን የስጋ ምኞታችንን በመቆጣጠር ራሳችንን የምንገዛ ሆነን እንድንገኝ የነፍሳችንን ጥሪና ተልዕኮ ለማወቅ ከመንፈስ ቅዱስ ሀይል እንድናገኝ ሊረዳን የሚያስችል ሊሆን እንደሚገባ፤ ይህን ካደረግን በስውር ያየን አባት በግልጥ እንደሚከፍለን፤ በጥቅሉ በዚህ ምድር ላይ የሕይወታችን ትልቁ ተልዕኮ ከሚያልፍ ምድር ጋር የማያልፍ ይልቁንስ ወደ ልዑል ዙፋን የሚቀርብ መንፈሳዊ ሀብት ማከማቸት እንደሆነ፤ በዚህ ሁሉ ግን እግዚአብሔር ብቻችንን እንደማይተወን አውቀን በነገሬ ሁሉ እግዚአብሔር አብሮኝ አለ ብለን በማመን ከጭንቀት ነፃ የሆነ ኑሮ በአምላካችን ፊት እንድንኖር ነው።
ምዕራፍ 7 በሌሎች ላይ የሚደረግ ፍርድን መነሻ ያደርጋል። መፍረድ ለመፈረድ ያዘጋጃል። የሰዎችን ፀባይና ድርጊት በእግዚአብሔር
ቃል መርምሮ መፍረድና በራሳቸው በሰዎች ላይ መፍረድ ለየቅል እንደሆኑና ሰው ላይ መፍረድ እኔ ከሱ እሻላለሁ ከሚል ትምክህት የሚመጣ ክፉ ማንነት እንደሆነ ይነግረናል። በሉቃስ 18 ከ9 እስከ 14 ያለውን ከመረዳት ያለፈ በቂ መልስ አይገኝም። ፈሪሳዊው በቀራጩ ላይ በፈረደ ጊዜ ጌታ "ራሱን ከፍ የሚያደርግ ይዋረዳል ራሱን ግን የሚያዋርድ ከፍ ይላል " ብሏልና።
የእግዚአብሔር የሆነ በክርስቶስ ልጆቹ ለሆኑት ሁሉ የተዘጋጀ (available ወይም accessible) የሆነ ስጦታ እንዳለና ይህንን ፈጣሪ እንደሚፈልግ ለጠየቁ ሁሉ የሚሰጥ ከአባቶችም ሁሉ የበለጠ አባት በሰማያት ስላለን ብናንኳኳ ሊከፈትልን፣ ብንፈልግ ልናገኝ፣
ብንጠይቅ ሊሰጠን እንደሚችል ካሰረገጠልን በኋላ ያንኑ ልናደርግ እንደሚገባ ያስተምራል።
ምዕራፍ 7፥13-14፦ የመንገድ ትልቁ ጥቅም ወደፈለጉበት ማድረስ ነው ጥያቄው ያለው የመረጥነው መንገድ ምን ዐይነት ነው? ለሚለው ከወዲሁ መልስ ማግኘቱ ላይ ነው። ወደ ጥፋት የሚያመራውን ምቹውንና ሰፊውን ወይንስ ብዙ መሰናክል ያለበትንና ወደ ሕይወት የሚመራውን ጠባቡን መንገድ? (ሉቃስ 13:24) በሮም ዘመን ‘መንገዶች ሁሉ ወደሮም ያደርሳሉ’ ይባል ነበር፤ ሁሉም ወደዚያ መሄድም ይፈልግ ነበር። በዚያ ጳውሎስ በሮሜ መልዕክቱ (1፥21-27) እንዳለው ሰዎች ለራሳቸው አዕምሮና ርኩሰት የተሰጡበት፣ ክርስቲያኖች ለተራቡ አንበሶችና ነብሮች በሕይወት እያሉ የተሰዉበት የርኩሰት ስፍራ ነበር። ወደ አምላካችን መንግሥት መግቢያው መንገድ ጠባብ ቢሆንም ደቀመዛሙርቱን ኑ ብሎ የጠራው ጌታ ነው ተከተሉኝ እያለን ያለው።
ምዕራፍ 7፥ከ15-29 ስለ ሐሰተኛ መምህራንና ነቢያት ማንነትና በእምነት የሆነ ቃልና ስራ ስለሚያስገኘው ውጤት ይናገራል። በዚህ በመጨረሻው ዘመን በግልጽ እየታዩ ካሉት ምልክቶች ዋንኛው ለእግዚአብሔር ቃል ከአውዱና ከተፃፈበት አላማ ውጭ የሆነ ትርጓሜ እየተሰጠ ለብዙዎች ከጠባቡ መንገድ ማፈንገጥ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ጌታችን ቀድሞ ተናግሯል። ስለዚህ ተጠንቀቁ ፍሬያቸው ከመልካም ወይንም ከክፉ ዛፍ መለቀሙን መርምሩ። ክፉው ፍሬ ወደ እሳት ይጣላልና፤ ጌታም በቀኑ መጨረሻ ለመልካሙና ለክፉም የሚሆን ፍርድ እሰጥ ዘንድ መንሹ በእጄ አለ ይለናል። እኛ ግን የመልካሙን የሕይወት ዛፍ ፍሬ መርጠን ቃሉንም በጥንቃቄ እየሰማን አድርጉ የተባልነውን እያደረግን የእግዚብሔር በሆነ መንፈስ በጥንቃቄ መኖር አለብን የጌታ ፀጋም አብሮን ስላለ በዚህ ፀጋ በመደገፍና ቃሉን ሰምተን አድራጊዎች በመሆን ቤታችንን በአለቱ በጌታ ላይ እንመሠርታለን፤ ይህ ከሆነ ማንኛውም ፈተና ወይም የትኛውም ሀይል አያፈርስብንም። ከክርስቶስ ፍቅር ሊለየኝ የማይችል አንዳችም ሃይል እንዳይኖር አውቃለሁ እንዳለው ሐዋርያው።
Comments